በደቡብ ክልል ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዝ 6ሚሊዮን 500ሺህ ብር ተሰበሰበ

83

ሀዋሳ ፣መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እንዲያገዝ በተደረገው ጥረት እስካሁን 6 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር መሰብሰቡን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ፡፡

በሌላ በኩል በሀዋሳ ከተማ የባለሁለት እግር ሞተር ብስክሌት እንቅስቃሴ መታገዱም ተገልጿል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በበሽታው መከላከል ሂደት የገንዝብ እጥረት እንዳያጋጥም በክልሉ የተቋቋመው ግብረ-ኃይል ሀብት የማሰባሰብና ሌሎች ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

እስካሁንም በገንዘብ 6 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

በተጨማሪ የህክምና ተቋማቸውን ፣ ሆቴላቸውንና መኖሪያ ቤታቸውን ለዚህ ዓላማ ያዋሉ ባለሀብቶች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

በየአካባቢውም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በጋራ እያከናወኗቸው ያሉ በጎ ተግባራት መኖራቸውንም አቶ ርስቱ አስረድተዋል።

"ይህንን ወረርሽኝ ማቆም እንችላለን የሚል የጋራ አቋም ይዘን በመከላከል ዘመቻው ላይ የሚጠበቅብንን ልንወጣ ይገባል” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በሀዋሳ ከተማ በሽታውን ለመከላከል የባለሁለት እግር ሞተር ብስክሌት እንቅስቃሴ መታገዱን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ገልጸዋል።

ቀደም ባሉ ቀናት በተደረጉ ክልከላዎች ባለሁለት እግር ሞተር ብስክሌለቶች ከአሽከርካሪው ውጭ ተጨማሪ ሰው ጭነው እንዳይንቀሳቀሱ ተደርጎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ብሎም ከአጎራባች ወረዳዎች የሚመጡ ሞተር ብስክሌቶች በከፍተኛ ሁኔታ እንቅስቃሴ የሚያደርጉባት መሆኑን ጠቁመው ይህ ደግሞ የሰው ለሰው ግንኙነትና ንክኪዎችን በማብዛት ቫይረሱ በፍጥነት እንዲዛመት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

በዚህ ምክንያት በሽታውን ለመከላከል በከተማዋ ከዛሬ እኩለ ቀን ጀምሮ የባለ ሁለት እግር ሞተር ብስክሌቶች እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ መታገዱን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም ከዛሬ ጀምሮ ሁሉም መጠጥ ቤቶች ዝግ እንዲሆኑ የከተማ አስተዳደሩ መወሰኑን ምክትል ከንቲባው አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ በከተማዋ ሰኞ እና ሐሙስ ቀናት ባሉ ገበያዎች ሲጠቀም በመጠንቀቅ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት ጠቁመው በእነዚህ ሁለት ቀናት ሰፊ ግብይት እንዳይከናወንባቸው የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።

የግንዛቤ መፍጠር ስራዎች ቢኖሩም በህብረተሰቡ ዘንድ አሁንም በመዘናጋት የተለመደው ዓይነት እንቅስቃሴ በመቀጠሉ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳሰበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም