በአዳማ ከተማ አንድ ባለሃብት ባለ ስምንት ፎቅ ህንፃቸውን ለኮሮና መታከሚያ እንዲሆን አስረከቡ

75

አዳማ መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ) በአዳማ ከተማ አንድ ባለሃብት ባለ ስምንት ፎቅ ሆቴላቸውን ለኮረና ቫይረስ ህሙማን መታካሚያ እንዲውል ለኦሮሚያ ጤና ቢሮ አስረከቡ ።

አቶ አብይ አበበ የተባሉ ባለሃብት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን  ለመከላከል  የክልሉ  መንግስት  የሚያደርገውን ጥረት ለማጋዝ  ሆቴሉ ለለይቶ ማቆያና  ለማከሚያ  አገልግሎት  እንዲውል መወሰናቸውን ገልጠዋል።

ሀገርና መንግስትን የሚፈታተን ችግር ከገጠመን መጋፈጥ ያለብን እኛው ባለሃብቶች ነን ያሉት አቶ አብይ በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት ቲታስ እንተርናሽናል  የተባለውን  ባለ ስምንት ፎቅ   ሆቴል  ለክልሉ  ጤና ቢሮ አስረክበዋል ።

ባለ ስምንት ወለል ህንፃው እስከ 300 አልጋ የሚይዝ ነው ያሉት ባለሃብቱ ከህዝብና ከሀገር በላይ የሚጠብቀው ትርፍ ባለመኖሩ በፈቃዴ ሰጥቻለሁ ብለዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው አዳማ ከተማ ከአዲስ አበባ ቀጥላ የኮረና ቫይረስ ታማሚዎች የተገኙባት በመሆኑ ወራርሽኑ ስጋት መፍጠሩን ተናግረዋል ።

የከተማዋና አካባቢዋ ባላሃብቶች ይህን ተገንዝበው የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚደረገው ጥረት በአይነትና በገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጠዋል።

አቶ አብይ አበበ በወር 4 ሚሊዮን ብር የሚያገኙበትን ሆቴል ለኮሮና ቫይረስ መታከሚያ ጊዜያዊ ሆስፒታል እንዲሆን ማስረከባቸው የድጋፉ አንዱ ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።

ሀገር ማለት ሰው መሆኑን የተረዳው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህን አስከፊ በሽታ ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ባለው አቅም ሊያግዘን ይገባል ያሉት ደግሞ ህንፃውን በአዳማ ተገኝተው የተረከቡት የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ናቸው።

በከተማዋም ሆነ በክልሉ በበሽታው የተፈጠረውን ስጋት ለመቀነስና የቫይረሱን  ስርጭት  ለመቆጣጠር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ባለው አቅምና ጉልበት ከጎናችን መቆም አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም