ኢትዮጵያ ሰፊ ምጣኔ ሃብታዊ እርምጃዎች እየወሰደች ነው ተባለ

62

መጋቢት 24/2012(ኢዜአ)የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመላው አለም መከሰትን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ዋና ዋና የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን ፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ሊቀመንበር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ተናገሩ።

ከባንኮች ተበድረው ስራቸውን የሚያስኬዱ የንግድ ድርጅቶችና ወጣት ስራ ፈጣሪዎች አሁን ካጋጠመው ምጣኔ ሃብታዊ መቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ የሚደርስባቸውን ጫና ለመቀነስ መንግስት ከግል ባንኮች ጋር በማስተሳሰር ስራ ሰርተው በተራዘመ ጊዜ የእዳ ክፍያቸውን እንዲያጠናቅቁ ማሰቻል የመጀመሪያው መሆኑን ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።

በርካቶቹ የኢትዮዽያ የግል ባንኮች ቀደም ብለው የብድር ወለድ መጠናቸውን በመቀነስ፣ አዳዲስ አሰራሮችን በማስተዋወቅ ደምበኞች የሚያበዙባቸውን ስልቶች አውጥተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ዘመዴነህ አክለውም ይሄ አይነቱ የመንግስት እርምጃ ባንኮቹ ያለቸውን አቅም እንዲያጠናከሩ ከማገዙም በላይ የሚበላሽባቸውን የብድር መጠንም እንዲቀንስላቸው ያደርጋል ብለዋል።

ሃብታም ሃገራትም እያስተገበሩት ያሉት የምጣኔ ሃብት መታደጊያ ተጨማሪ በጀት መመደብን በሁለተኝነት ያነሱት ሊቀመንበሩ አሜሪካ ሁለት ትሪሊየን ዶላር መድባ እየተንቀሳቀሰች ሲሆን ኢትዮዽያም 15 ቢሊዮን ብር በመመደብ ምጣኔ ሃብቱን ከውድቀት ለመከላከል እየሰራች ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የኢትዮዽያን አበቦች በከፍተኛ ደረጃ ሲቀበሉ የነበሩት ሆላንድን የመሳሰሉት ሃገራት አሁን ላይ አበባ የመግዛት ፍላጎት ባለማሳየታቸው በኢትዮዽያ ያሉ አምራቾች ኪሳራ ውስጥ መውደቃቸውን የሚያነሱት አቶ ዘመዴነህ፤ ኢትዮዽያም በዚህ ዘርፍ የምታገኘውን ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ማጣቷን አስረድተዋል።

ኮቪድ-19 በተከሰተባቸው ሃገራት ከፍተኛ ፍርሃት በመንገሱ የንጽህና መጠበቂያዎችና የምግብ ፍጆታዎች እንደበፊቱ ከገበያ ሊገኙ ያለመቻላቸውን ያስረደት ሊቀመንበሩ፤ በኢትዮዽያም ተመሳሳይ ክስተት ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት የምግብ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማጋጠሙን አንስተዋል።

ሌሎች ታዳጊ ሃገራት እንዳደረጉት ሁሉ ኢትዮዽያም የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን ኑሮ ለማረጋጋት በሚል በንግድ ሚኒስቴር በኩል የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው ብለዋል።

ሊቀመንበሩ ኮቪድ 19ን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይረዳሉ የሚባሉ የህክምና ግብአቶችንና መሳሪያዎችን የሚያመርቱና ወደ ሃገር ውስጥ የሚያስገቡ ኩባንያዎችን ለማበረታታት በሚል መንግስት ላልተወሰነ ጊዜ ተግብር እፎይታ ስለመስጠቱ ተናግረዋል።

በጠ/ሚ/ አብይ በኩል የአፍሪካን ምጣኔ ሃብት ለመታደግ የሚረዳ የ150 ቢሊየን ዶላር ጥያቂ መቅረቡ አሳማኝና ወቅቱን ያገናዘበ ነው ያሉት አቶ ዘመዴነህ፤ አብዛቹ እዳ ያለባቸው የአፍሪካ ሃገራት 10 በመቶ የሚሆነውን አመታዊ በጀታውን ለእዳ ክፍያ እንደሚያውሉት ተናግረዋል።

የቡድን ሃያ ሃገራት የአለም ባንክና የአለም የገንዘብ ድርጅት አፍሪካ ያጋጠማትን ፈተና ከግምት ውስጥ በማስገባት የእዳ ክፍያ ጊዜዎቹን በማራዘም እንዲሁም ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ምጣኔ ሃብቷ እንዲያንሰራራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮዽያ መንግስት የወሰዳቸው አነዚህ የማስተካከያ እርምጃዎች ውጤታማ እንደሚሆኑም ያላቸውን ተስፋ ለሲ.ኤን ቢ ሲ አፍሪካ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም