ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ደብቆ ተገኘ የተባለ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

63

ደብረማርቆስ መጋቢት 24 /2012 (ኢዜአ) በደብረማርቆስ ከተማ 39 ሽጉጦችና በርካታ ጥይቶች በመኖሪያ ቤቱ ደብቆ የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የከተማዋ ፖሊስ ገለፀ ።

በደብረማርቆስ ከተማ 1ኛ ፖሊስ ጣቢያ የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ታዬ ሞሴ ለኢዜአ እንደገለፁት ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው ትናንት 10 ሰዓት አካባቢ በከተማዋ ቀበሌ 04 በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ነው ።

በህብረተሰቡ ጥቆማ መሰረት ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ሲውል 21 የሚሰሩና ለጥገና በሚል ሰበብ 18 የማይሰሩ ሽጉጡች በመኖሪያ ቤቱ ተገኝቷል ።

በተጨማሪም 108 የሽጉጥና 634 የክላሽ ጥይቶች የተገኘ ሲሆን ሌሎች የጥይት መያዣ ካዝናዎችም አብረው ተይዘዋል ።

በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የተጠረጠረው ግለሰብ ጉዳዩ በህግ ተይዞ የማጣራት ስራው እየተካሔደ መሆኑን አስረድተዋል ።

ህብረተሰቡ የራሱንና የአካባቢውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ከፀጥታ አካላት ጋር የጀመረውን ትበብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ዋና ኢንስፔክተሩ መልእክት አስተላልፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም