የቡደን 20 አባል አገራት ለአፍሪካ የድጋፍ ፓኬጅ እያዘጋጁ ነው

59

አዲስ አበባ፣መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ) የቡድን 20 አባል አገራት የአፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስን ተጽዕኖን መቋቋም የሚችሉበት የድጋፍ ፓኬጅ እያዘጋጁ መሆኑ ታወቀ።

የድጋፍ ፓኬጁ ለአፍሪካ አገራት ቀደም ሲል የተሰጡ ብድሮችን ክፍያ ማዘግየትና የገንዘብ ድጋፍ ማድረግን ያካተተ ነው።     

የኮሮናቫይረስ መነሻውን ቻይና በማድረግ በርከታ የአውሮፓ አገራትን ያደረሰ በሽታ ነው።     

ቫይረሱ በአፍሪካ ያለው ተጽዕኖ ከሌሎች የአውሮፓ አገራት ጋር ሲነጻጸር ያነሰ ቢሆንም አፍሪካ ካለችበት የጤናና የኢኮኖሚ ሁኔታ ሲታይ ተጽኖው የከፋ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።  

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው ትንበያ እንደሚያሳየው ዓመታዊ የአፍሪካ አገራት ምርት(ጂ ዲፒ) 3 ነጥብ 2 በመቶ ከነበረበት በበሽታው ምክንያት ወደ 1 ነጥብ 8 በመቶ ዝቅ ሊል ይችላል።  

ይህንን ከግምት በማስገባትም የአፍሪካ አገራት መሪዎች የበለጸጉ አገራት ድጋፍ ጥሪ እያቀረቡ ሲሆን ጥሪው የበለጸጉት አገራት በዓለም ባንክ፣ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋምና በአፍሪካ ልማት ባንክ በኩል ገንዘብ እንዲደጉሙ የሚጠይቅ ነው።     

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ያቀረቡትን የድጋፍ ጥሪ ተከትሎ የቡድን 20 አባል አገራት የድጋፍ ፓኬጅ እያዘጋጁ እንደሆነ ነው ፖለቲኮ የተባለው ጋዜጣ ያስነበበው።  

የአፍሪካ ኀብረት ሊቀ-መንበር ቃል ቀባይ ኢባ ካሎንዶ በሰጡት አስተያየት ''የድጋፍ ጥሪው የእርጥባን ጉዳይ ሳይሆን እንደሰው በጋራ የመቆም ጉዳይ ነው፤ በዚህ ከባድ ወቅት ወንድማማችነት ማሳየት ከየትኛውም የፖለቲካ ጉዳይ ጋር ሊያያዝ አይችልም ነው'' ያሉት። 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው በድጋፍ ፓኬጅ ዙሪያ ዓለም አቀፍ ስምምነት እየጎለበተ መምጣቱን ተናግረዋል።   

በዚህ ወቅት ብድር መመለስ አስቸጋሪ መሆኑን የገለጹት አማካሪው አበዳሪዎች ወቅቱን ተገንዝበው ለጊዜው የብድር ክፍያን እንዲያቆሙ ግፊት እያደረግን ነው ብለዋል።      

አፍሪካ ድጋፍ ካልተደረገላት የኢኮኖሚው ቀውስ፣ የገንዘብና የስራ አጥነት ቀውስ የሚሊዮኖችን ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ጉዳዩ አጽንኦት የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል።

የቡድን 20 አባል አገራት ባለፈው ሳምንት 5 ትሪሊዮን ዶላር ወደ ዓለም ኢኮኖሚ ግብይት ማስገባታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም