የምሩቃን ተማሪዎችን የሥራ አጥነት ችግር ለማቃለል እየሰራ መሆኑን የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ

83
ሐረር ሰኔ 24/2010 የምሩቃን ተማሪዎችን የሥራ አጥነት ችግር ለማቃለል በሥራ ዕድል ፈጠራና መሰል ተግባራት ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎችን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር  የሚያገናኝ የሥራ እድል ትስስር አውደ ርዕይ በማዘጋጀት ትውውቅ አድርጓል። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ በእለቱ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ከማሰልጠን ጎን ለጎን በሥራ ዕድል ፈጠራና በንግድ ክህሎት ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኙ ስልጠና ይሰጣል። ለእዚህም በዩኒቨርሲቲው ሥራ ተኮር የምክር አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በማቋቋም ተማሪዎች ሥራ ጠባቂ ሳይሆን ሥራ ፈጥረው እንዲንቀሳቀሱና በእዚህም ሊያጋጥማቸው በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የምክር አገልግሎት እንደሚሰጥ አስረድተዋል። እንደ ፕሮፌሰር ንጉሴ ገለጻ ተመራቂ ተማሪዎችንና የቀጣሪ ድርጅትን ትስስር ለማጠናከር ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ የሥራ ዕድል አውደ ርዕይ አዘጋጅቷል። "ይህም ሁለቱም ወገኖች መረጃ እንዲለዋወጡና ወደ ሥራው አለም በቀላሉ ተግባብተው እንዲገቡ ያስችላል" ነው ያሉት። ከእዚህ በተጨማሪ ቀጣሪ ድርጅቶቹ በተማሪዎቹ ላይ የሚታየውን የአካዳሚክ ክፍተት ለተቋሙ በመስጠት በቀጣይ መስተካከል ያለበትን በቀላሉ ማግኘት እንደሚያስችልም ተናግረዋል። ከዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ በኢኮኖሚክስ በመጀመርያ ዲግሪ  የምትመረቀው ተማሪ ፌቨን ፈለቀ እንዳለችው ዩኒቨርሲቲው በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ስልጠና መስጠቱንና አውደ ርዕይ ማዘጋጀቱ በቀጣይ ወደሥራ እንዲገቡ በማድረግ በኩል ጠቀሜታው የጎላ ነው። በተለይ በአውደ ርዕዩ ላይ የተለያዩ ቀጣሪ ድርጅቶች ተገኝተው ስለተቋማቸውና ስለሚፈልጉት የሰው ኃይል ገለጻና ማብራሪያ መስጠታቸው ከምረቃ በኋላ ሥራ የማግኘት ዕድላቸውን እንደሚያሰፋው አስረድታለች። "አውደ ርዕዩ ድርጅቶች የሚፈልጉትን የተማረ የሰው ኃይል በቀጥታ እንዲያገኙ፣ ለቅጥር አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉና ከቀጣሪ ተቋማት ጋር በመረጃ የተሳሰረ ግንኙነት ለመፍጠር ያግዘናል" ያለው ደግሞ የኤሌትሪካልና ኮምፒውተር ኢንጅነሪንግ ተመራቂ ተማሪ ፉፋ ኡመታ ነው። በአውደ ርዕዩ ላይ ከተገኙት ቀጣሪ ድርጅቶች መካከል የቻይና ሲቪል ኢንጅነሪንግ ኮንስትራክሽን የሰው ሀብት ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዩሐንስ በዛብህ  እንዳሉት፣ በመረጃ የጎለበተ ወጣት የሰው ኃይልን መቅጠር ጠቀሜታው የጎላ ነው። ድርጅታቸው በምህንድስና ዘርፍ ዘንድሮ የሚመረቁ በርካታ ተማሪዎችን እንደሚቀጥር ገልጸው፣ በአውደርዕይ ተማሪዎችን ከቀጣሪዎች ጋር የማገናኘቱ ሂደት በሌሎች ተቋማትም ሊለመድ ይገባል" ብለዋል። " ከዚህ ቀደም ከተቋሙ የተመረቁ ተማሪዎችን ወስደን ቅጥር ፈጽመናል፤ አሁንም ለመዘገብናቸው ተመራቂዎች ገለጻ በመስጠት ቅጥር እንፈጽማለን" ያሉት ደግሞ  የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ካምፓኒ የድሬዳዋ የሰው ኃይል አስተዳደር ወይዘሮ ሀና አይሳ ናቸው። ወጣቶችን መቅጠር የትም ሄደው መስራት፣ መማርና መለወጥ ስለሚችሉ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም አስረድተዋል። በአውደ ርዕዩ  ላይ የቻይና ሲቪል ኢንጅነሪንግ ኮንስትራክሽን፣ የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ካምፓኒና የምርት ገበያን ጨምሮ 20 ቀጣሪ ድርጅቶች ተገኝተው የተመራቂ ተማቂዎችን የትምህርት መረጃና የሥራ መጠየቂያ ፎርም ወስደዋል። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ በመደበኛ የትምህርት መርሀ ግብር በመጀመርያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 4 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ያስመርቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም