በአራት የክልል ከተሞች በቅርቡ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ይጀመራል - የጤና ሚኒስቴር

87

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2012( ኢዜአ) በአራት የክልል ከተሞች በቅርቡ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) የላቦራቶሪ ምርመራ እንደሚጀመር የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

በአዲስ አበባ በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ብቻ ይደረግ የነበረው የኮሮናቫይረስ ምርምራ አሁን ላይ ወደ ሶስት ከፍ ብሏል።

ከኢንስቲትዩቱ በተጨማሪ በአርማወር ሀንሰን ምርምር ኢኒስቲትዩት እና ሰበታ በሚገኘው የብሔራዊ እንስሳት ጤና ምርምርና ጥናት ማዕከል(ናዲክ) በአዲስ አበባ የቫይረሱ ምርመራ እየተከናወነ ይገኛል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ላቦራቶሪ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአራት የክልል ከተሞች በቅርቡ ይጀመራል።

በክልሎች ቫይረሱን ለመከላከል ያለው የዝግጅት መጠን እያደገ መሆኑንና የለይቶ ማቆያ ማዕከላትን የማስፋት፣ ባለሙያዎች የማሰልጠንና የምርምራ ላብራቶሪዎችን የማዘጋጀት ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የለይቶ ማቆያ ቦታዎች እየተዘጋጁ እንደሆነና የትኞቹ ማዕከላት ለየትኛው ተግባር ይውላሉ የሚለው ጉዳይ በቅርቡ በዝርዝር እንደሚገለጽም አመልክተዋል።

በመዲናዋ የኮሮናቫይረስ ከያዛቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች የሚለዩ ቡድኖች ቁጥር እያደገ ሲሆን በክልሎችም እንዚህን ቡድኖች የማስፋት ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ለኮሮናቫይረስ ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ ቡድኖች ከ28 ወደ 32 ከፍ ማለቱን ያስታሱት ዶክተር ሊያ በቅርቡም ወደ 38 ያድጋል ብለዋል።

ከግብአት ጋር በተያያዘ ለቫይረሱ ህክምና የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ለክልሎች ተደራሽ የማድረግ ተግባር መቀጠሉንና ዛሬና ነገ በክልሎች ተጨማሪ ግብአቶች ይሰራጫሉ ብለዋል።

የግብአት እጥረትን ለመፍታት በግዥ የሚመጡትን የማፋጠንና በእርዳታ የተገኙትን በፍጥነት የማሳበሰብ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የእምነት ተቋማት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እየወሰዱት ያለውን ተግባርም ሚኒስትሯ አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) የተያዙ ሰዎች ቁጥር 29 የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ሶሰት ሰዎች አገግመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም