የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ኮሮናን ለመከላከል እንዲያግዝ አምስት ሚሊዮን ብር ለገሰ

74

አሶሳ፣ መጋቢት 24 / 2012 (ኢዜአ) የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እንዲያግዝ የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

የክልሉ ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረኃይል ዩኒቨርሲቲው ለበሽታው መከላከል ያደረገውን ጥረት በግቢው ተዘዋውሮ ጎብኝቷል፡፡

በዚሁ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ከማል አብዱራሂም እንደገለጹት የዩኒቨርሲቲው  የመማር ማስተማር ሂደቱ  የሚሳካው የማህበረሰቡ ደህንነት ሲጠበቅ ነው፡፡

ይህንን መሠረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አምስት ሚሊዮን ብር ለኮሮና ቫይረስ መከላከል ድጋፍ እንዲውል መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡

በሽታው በክልሉ ቢከሰት ለምርመራ፣ ህክምና እና ለይቶ ማቆያ እንዲሆን የዩኒቨርሲቲውን አምስት ህንጻዎች ማመቻቸታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ከ7 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎች በቅርቡ ወደ ቤተሰቦቻቸው መሸኘታቸውን ያስታወሱት ዶክተር ከማል ለተማሪዎች ሲሰጥ የነበረውን የዩኒቨርሲቲው የመጠጥ ውሃ ለከተማው ማህበረስብ እንዲውል መወሰኑንም አስታውቀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለችግረኛ ወገኖች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የግብረ ኃይሉ አባልና የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ ዩኒቨርሲቲው  ለህክምና የሚውል ህንጻ ብቻ ሳይሆን ባለሙያዎቹ ጭምር ድጋፍ እንዲሰጡ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

ለድጋፉ ምስጋናቸውን አቅረበው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እና ማኔጅመንት የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ያደረጉት እገዛ  ሌሎችም አርአያነቱን  እንዲከተሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

"በክልሉ በሽታውን በመከላከል ረገድ ገና ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል " ያሉት ደግሞ  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አቶ አሻድሊ ሃሰን ናቸው።

መከላከሉ ካልተጠናከረ ቫይረሱ የሚያስከትለውን ጉዳት አብራርተው "እንደ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ባለድርሻ አካላት ለመከላከል ሥራው ርብርባቸውን ካጠናከሩ በሽታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንቆጣጠራለን" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም