የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 9ኛ ዓመት በፓናል ውይይት እየተከበረ ነው

98

አዲስ አበባ፣መጋቢት24/2012 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት 9ኛ ዓመት በአዲስ አበባ በፓናል ውይይት እየተከበረ ነው።

የፓናል ውይይቱ በግድቡ ዙሪያ ያሉ ወቅታዊና አዳዲስ መረጃዎችን ለህዝቡ ለማድረስ እንዲሁም በመንግስት በኩል ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ዓላማ ያደረገ መሆኑ ታውቋል።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ የውይይቱ ተሳታፊዎች ናቸው።

በውይይቱ መክፈቻ ላይ የኘሮጀክቱ ሂደት አሁናዊ የአፈፃፀም ደረጃ ከ72 ነጥብ 4 በመቶ በላይ መድረሱ ተገልጿል ።

ለግድቡ ግንባታ እስካሁን ከህዝቡ ወደ 13.4 ቢሊዮን ብር በድጋፍ መልክ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ደግሞ የጉልበት ድጋፍ ተደርጓል ተብሏል።

ከለውጡ በኋላ በተሰጠ ጠንካራ አመራር ለስድስት ዓመታት የዘገየውን የግንባታ ሂደት በፍጥነት እንዲከናወን በማድረግ ከወራት በኋላ የውሀ ሙሌት እንደሚጀምር በውይይቱ ላይ ተገልጿል።

በታህሳስ 2013 ዓ.ም የግድቡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት የሚጀምሩ ሲሆን ግንባታውም ሲጠናቀቅ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የሚይዝ ይሆናል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠው መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም