ዋተርኤይድ ኢትዮጵያ የኮሮናን ስርጭት ለመከላከል የ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

150

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2012 (ኢዜአ) ዋተርኤይድ ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል መንግስት እያከናወነ ያለውን ተግባር ለማከናወን የ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ።

ዋተርኤይድ ኢትዮጵያ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ድጋፉን ለውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስረክቧል።

ተቋሙ 5ሺህ ሊትር የመያዝ አቅም ያላቸው የውሃ ጋኖች፣ 2ሺህ 500 ሊትር አልኮሆል እና ከ1ሺህ እሽግ በላይ የላውንደሪ ሳሙና ለአዲስ አበባ ጤና ጣቢያዎችና በጊዜያዊነት የኮሮናቫይረስ ተጠርጣሪዎች ለይቶ ማቆያዎች ለግሷል።

ከዚህ በተጨማሪም ስለ ንጽህና አጠባበቅ ትምህርት የሚሰጡ የቅስቀሳ ቪዲዮዎችና የድምጽ መልዕክቶችን ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አሰራጭቷል።

መልዕክቶቹ ህብረተሰቡ እጁን በአግባቡ እንዲታጠብና ሌሎች ከኮሮናቫይረስ ስርጭትን መጠበቅ የሚያስችሉ መሆናቸውን ዋተርኤይድ ኢትዮጵያ ገልጿል።

ንጽህና መጠበቅ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ተቋሙ የኮሮናቫይረስ መከላከያ መንገድ የሆነው የእጅ መታጠብ ተግባር ከዓላማው ጋር አብሮ የሚሄድ በመሆኑ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥልበት አስታውቋል።

በተለይም በጤና ተቋማት የሚያጋጥመውን የግብዓት እጥረት ለመፍታት የሚሰራ መሆኑን ገልጿል።

ድጋፉን የተቀበለው የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በበኩሉ ዋተርኤይድ ላደረገው ድጋፍ በመንግስት ስም ምስጋናውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም