በኦሮሚያ ባለሀብቶች ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

92

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2012  (ኢዜአ) 23 ባለሀብቶች በኦሮሚያ ክልል ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚውል የ41 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚያግዙ ግምታቸው 15 ሚሊዮን ብር የሆኑ ግብአቶች ለክልሉ ድጋፍ አድርጓል።

ባለሀብቶቹ ዛሬ በኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ተገኝተው የገንዘብ ቼኩን ለክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስረክበዋል።

ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ ባለሀብቶቹ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ለሚሰራው ስራ የተሽከርካሪ ድጋፍና የለይቶ ማቆያ ቦታ እንዳስረከቡ ተገልጿል።

አቶ ሽመልስ ''የተደረገው የፋይናንስ ድጋፍ በክልሉ የተጀመረውን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን የመግታትና የመቆጣጠር ጥረት ያግዛል'' ብለዋል።

የክልሉ ፕሬዚዳንት ባለሀብቶቹ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ ''አሁን በምንገኝበት ወሳኝ ጊዜ የገጠመንን ፈተና ለማለፍ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋል'' ሲሉ ገልጸዋል።

ኮቪድ-19 የህዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የገለጹት አቶ ሽመልስ፤ ከዚህም አኳያ የተደረገው ድጋፍ ባለሀብቶቹ በልማቱ እያበረከቱት ካለው ወሳኝ አስተዋጽኦ ባለፈ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውንም የተወጡበት እንደሆነ አመልክተዋል።

ባለሀብቶች በበኩላቸው የኦሮሚያ ክልል የኮሮናይረስ ስርጭትን ለመግታትና ለመቆጣጠር እያደረገው ያለውን ጥረት መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ሁሉም ዜጋ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የቁሳቁስ፣ የፋይናንስና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት የማገዝ ሃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

ዛሬ በባለሀብቶቹ የተደረገው ድጋፍ የመጀመሪያ ዙር የፋይናንስ ድጋፍ እንደሆነና ሌሎች በክልሉ የሚገኙ ሌሎች ባለሀብቶች ድጋፍ ማድረግ እንደሚፈልጉ በድጋፉ ስነ ስርአት ወቅት ተገልጿል።

በተያያዘም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 15 ሚሊዮን ብር የሚገመት የመከላከያ ቁሳቁሶች፣ የእጅ ማጽጃ ኬሚካል (ሳኒታይዘር) እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለክልሉ አስረክቧል።

የኦሮሚያ ክልል የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ለሚያከናውናቸው ስራዎች ስምንት ኮሚቴዎችን ተቋቁመው እየሰሩ የሚገኝ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ሀብት የሚያሰባስበው የዜግነት አገልግሎት ኮሚቴ ይገኝበታል።

ኮሚቴው ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ እስካሁን የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ለሚውሉ ስራዎች 46 ሚሊዮን ብር ያህል ማሰባሰቡ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም