የመንግስት ሰራተኞች ባሉበት ቦታ ሆነው ስራቸውን ለመስራት የሚያስችል ቋሚ አሰራር እየቀመርን ነው ... ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን

123

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2012( ኢዜአ) የመንግስት ሰራተኞች ባሉበት ቦታ ሆነው የተጣለባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል አሰራር እየቀመረ መሆኑን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት፤ "ኮሚሽኑ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የፌዴራል ሰራተኞች ከቤታቸው ሆነው ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተወስኖ ተግባር ላይ የዋለውን አሰራር እንደተሞክሮ እያየው ነው" ብለዋል።

ሁሉም የመንግስት ስራዎች በየትኛውም ቦታ ሆነው የሚተገበሩ ባይሆኑም በርካታ ስራዎች ግን ሰራተኛው ባለበት ሆኖ መከወን የሚችላቸው መሆኑም ተጠቅሷል።

አሰራሩ የመንግስት ሰራተኛው የስራ ተነሳሽነት በማሳደግ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም፣ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንን አጠቃቀም በማዘመንና በማጠናከር ከተተገበረ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

አሁን ያለው አሰራር በተለይ ሁሉም ሰው ቢሮ መግባት አለመግባቱን የመቆጣጠርና መሰል ተግባራት የሰራተኛው የአፈፃፀም ስነ ልቦና ላይ የራሱ ተፅዕኖ እንዳለውም ተናግረዋ።

በመሆኑም የመንግስት ሰራተኛው ለሙያው ታማኝ መሆኑን፣ ሃላፊነቱን ባለበት ቦታ መወጣት አለመወጣቱን በማየት "አዲሱን ተሞክሮ እያዬንና እየቀመርን ነው" ብለዋል።

"ዘመናዊ አሰራርን ከተገበርንና ግንኙነታችንን አጠናክረን ይህንን አሰራር የምንተገብር ከሆነ መንግስት ሁሉም ሰራተኛ በቢሮ እንዲሰራ ለማድረግ የሚያወጣውን የቢሮ ኪራይ ወጭ መቀነስ ይቻላል" ሲሉ ተናግረዋል።

የፌደራል መንግስት ተቋማት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የተወሰኑ ሰራተኞቻቸውን በቤታቸው ሆነው በመንግስት የሚሰጣቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ያደረጉ ሲሆን በዚሁ መሰረት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነሩ የተቋማትን አፈፃፀምና የስራ ሂደት እየጎበኙ ነው።

በጉብኝቱ የተቋማቱ የቢሮ ውስጥ የስራ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል፣ ተቋማቱ በቤታቸው ከሚሰሩ ሰራተኞቻቸው ጋር በምንና እንዴት እየተገናኙ ነው የሚለውን ከግንዛቤ ያስገባ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም