የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና ተጠሪዎቹ ከፍተኛ አመራሮች የወር ደመወዛቸው ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መከላከል እንዲውል ወሰኑ

96

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2012( ኢዜአ) የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች የአንድ ወር ደመወዛቸውን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከል እንዲውል ወሰኑ።

ሚኒስቴሩ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡

ይህንኑ ጥረት ለማገዝም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች የአንድ ወር ደመወዛቸውን ወረርሽኙን ለመከላከል እንዲውል ወስነዋል፡፡

የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ባካሄዱት ውይይት ሚኒስቴሩ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እያደረገ ካለው ጥረት ባሻገር የአንድ ወር ደመወዛቸውን የለገሱ ሲሆን ወረርሽኙን ለመግታት በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ የሚቻላቸውን እንደሚያደርጉ አመልከተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በከተሞች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ የሚያስችል መሪ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባቱን በመግለጫው ጠቁሟል።

''ዕቅዱን እስከ ክልል ከተሞች በማውረድ ትስስሩን በጠበቀ መልኩ ከፍተኛ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል'' ብሏል በመግለጫው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም