በደቡብ ክለል ለህዳሴው ግድብ የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ ነው

54

ሀዋሳ፤ መጋቢት 23/2012( ኢዜአ) በደቡብ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚደረገውን ድጋፍን አጠናክሮ ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ መሆኑን በክልሉ የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ገለጸ፡፡

የማስተባበሪያ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን ከበደ ለጋዜጠኞች እንዳሉት የግድቡ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት ዘጠነኛ ዓመት የሚከበረው ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ "ጤናችንን እንጠብቅ ግድባችንን እንጨርስ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።

በበሽታው ምክንያት በዓሉ በክልሉ የሚከበረው  ሁሉም በያለበት ነው ብለዋል።

በህዝብ ፍላጎትና ትብብር የሚገነባው ግድቡ  ብሔራዊ መግባባትን ከማጎልበት አኳያም የጎላ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት ዘጠነኛ ዓመት መከበሩ መሀል ላይ ተቀዛቅዞ የነበረውን የህዝብ ተሳትፎ በማነቃቃት ስራው በፍጥነት ተጠናቆ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል ህዝቦች ለግድቡ ግንባታ እስካሁን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ያስታወሱት አቶ ጥላሁን፤ እንደ ሀገር በተከናወነው የዋንጫ ማዞር ገቢ ማሰባሰብ መርሀ ግብር ክልሉ አንድ ቢሊዮን 600ሚሊዮን ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በተያዘው ዓመት እስከ የካቲት ወር ድረስ  ከክልሉ 43 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉንና  ይህም በብሔራዊ ደረጃ ከፍተኛ እንደሆነ  ገልጸዋል፡፡

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ ከነበረው ችግር ጋር ተያይዞ  የተስተዋለው መቀዛቀዝ አስተባባሪ ምክር ቤቱ ባደረገው ጥረት አብዛኛዎቹን መነቃቃት መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

ህዝቡም በእኔነት ስሜት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ጥላሁን፤ ህብረተሰቡን ከዚህ በበለጠ ለማሳተፍ የንቅናቄ ሥራዎች እንደሚቀጥሉነው የተናገሩት። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ የተጣለበት ዘጠነኛ ዓመት የሚሆነው መጋቢት 24/2012 ዓ.ም መሆኑ ይታወቃል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም