ከለውጡ በኋላ የተወሰዱ የማሻሻያ ርምጃዎች ግድቡ በተሻለ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አድርጓል ... ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ

69

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2012  (ኢዜአ) ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች ግድቡ በጥሩ ደረጃ ላይ እንዲገኝ ማድረጉን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ። 
በመጪው ክረምት ግድቡ ውሃ መያዝ እንደሚጀምርም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።   

የግድቡ ግንባታ መሰረት የተጣለበትን 9ኛ ዓመት አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንደገለጹት፤ ግድቡ ገጥሞት ከነበረው ችግር በተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በተለይም የዋናው ግድብ፣ የኮርቻ ግድብ፣ የጎርፍ ማስተንፈሻ አካል፣ የኃይል ማመንጫ ቤቶችና ኃይል መቀበያ አጠቃላይ የሲቪል ስራዎች ከነበረበት 80 በመቶ ወደ 86 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት ግድቡ 72 ነጥብ 4 በመቶ መድረሱን ነው ሚኒስትሩ ያመለከቱት።  

እንደ ዶክተር እንጂነር ስለሺ ገለጻ፤ የግድቡ የብረታ ብረት ስራዎች 13 ነጥብ 86 ከመቶ የነበረ ሲሆን ያሉበት የጥራት ችግሮች እንዲስተካከሉ ተደርጎ በአሁኑ ወቅት ስራው 20 ነጥብ 4 በመቶ ደርሷል።   

የተርባይንና ኃይል መቀበያ ማከፋፈል ስራዎችም ከ25 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 44 ነጥብ 3 በመቶ ማደጉን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከጉባ በመነሳት ሆለታ ላይ የሚያገናኘው የ500 ኪሎ ቮልት የትራንስሚሽን ሲስተም ዝግጅት ከሁለት ዓመት በፊት መጠናቀቁን አረጋግጠዋል።   

''ግድቡ ውሃ እንዲይዝ የሚያስችለው የኮንክሪት ሙሌት ስራ በተያዘው ወር ተጀምሯል'' ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህ ስራ ተጠናቆ በመጪው ክረምት ግድቡ ውሃ መያዝ እንደሚጀምር ጠቁመዋል።

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የግድቡ ግንባታ እንዳይስተጓጎል ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ብሄራዊ ግብረ ኃይል እንደተቋቋመ ተናግረዋል።  

ግብጽ የግድቡ ግንባታ እንዳይሳካ ጉዳዩ የፖለቲካ ገጽታ እንዲኖረው ጥረት እያደረገች መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ''ኢትዮጵያ ግን መርህን ተከትላ በፍትሐዊነት ስለምትሰራ በድል ታጠናቅቃለች'' ብለዋል።

ኢትዮጵያ በስምራቅ አፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን እየተጋች መሆኑን ያብራሩት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፤ በትላንትናው ዕለት በኮርቤቴና ቱሉ ሞዬ ከጂኦ ተርማል 300 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት ከሁለት ኩባንያዎች ጋር ስምምነት መደረሱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ መሰረት ከተጣለበት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ህብረተሰቡ ሂደቱን በቅርብ እየተከታተለ ሲሆን ድጋፍ እያደረገም ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም