የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ኮሮናን ለመከላከል ውሳኔዎችን አሳለፈ

63

ጋምቤላ፤ መጋቢት 23/2012 (ኢዜአ) የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለ14 ቀናት ተፈፃሚ የሚሆኑ የተለያዩ ውሳኔዎች  ማሳለፉን አስታወቀ።  
 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ውሳኔዎቹ የተላለፉት የክልሉ መንግስት ካቢኔ ትናንት ባካሄደው ስብሰባ  ሲሆን ተግባራዊ የሚሆኑትም  ከመጋቢት 23/ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ነው።

በውሳኔው መሰረትም ከመሃል ሀገርና ከአጎራባች ክልሎች ወደ ክልሉ የሚገቡና የሚወጡ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል።

ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ በከተማ የህዝብ ትርንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ሚኒባሶች ሙሉ ለሙሉ ስራቸውን እንዲያቆሙ እንዲሁም  የሞተር ተሽከርካሪዎችም  ከአንድ ሰው ሌላ እንዳይጭኑ መወሰኑን አስታውቀዋል።

ከክልል ወደ ዞኖችና ወረዳዎች የህዝብ ትራንስፖርት አገልገሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ቀደም ሲል ሲጭኑ ከነበረው የሰው ቁጥር በግማሽ እንዲቀንሱ ገደብ ተጥሎባቸዋል።

የሺሻ፣ ጫት፣ ጭፈራና መጠጥ ቤቶች ለቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው በመሆኑ እንዲዘጉ መወሰኑንም ገልጸዋል።

ጫት ከአጎራባች አካባቢዎች ወደ ክልሉ እንዳይባ መከልከሉንም አመልክተዋል።

ከፍተኛ የሰራተኛ ቁጥር ባለባቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች በእድሜ የገፉ፣ ነፍሰጡርና የሚያጠቡ እናቶች ሥራቸውን በቤታቸው እንዲያከናወኑም ተወስኗል።

"በክልሉ የሚገኙ ስደተኞች እንደ ሀገር በሚሰጠው መመሪያ መሰረት ከአሁን በፊት ከነበራቸው ልቅ እንቅስቀሴ የሚገደቡ ይሆናል" ብለዋል።

ከበሽታው ጋር በተያያዘ የንግድ ማህበረሰብ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደረግ ክትትሉ እንዲጠናከር  መወሰኑንም አቶ ኡሞድ ተናግረዋል።

በክልሉ መንግስት የተላለፉት ውሳኔዎች  ተፈፃሚ እንዲሆኑ ለጸጥታ አካላት መመሪያ መተላለፉንም  ርዕሰ መስተዳደሩ በመግጫቸው አስታውቀዋል።

መንግስት ላስተላለፋቸው ውሳኔዎች ተፈፃሚነት ሁሉም  ዜጋ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደረግም መልዕክታቸውን በማስተላለፍ፤ ውሳኔ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ሳምንታት እንደሚቆይም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም