የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ስለኮሮናቫይረስ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ አከናወኑ

92

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2012( ኢዜአ) የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ በሚስተዋልበት መርካቶ አካባቢ በመዘዋወር ነው ስለኮሮናቫይረስ መከላከያ መንገዶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ያከናወኑት። 

አቶ መላኩ አለበል በቅስቀሳው ወቅት ነጋዴውና ሸማቹ ማህበረሰብ ራሱን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የጤና ባለሙያዎች የሚያስተላልፉትን የጥንቃቄ መልዕክት መተግበር እንዳለበት ገልፀዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በግብይት ወቅት መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎችም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተለይም ህብረተሰቡ በሚገበያይበት ወቅት ማህበራዊ ርቀቱን ጠብቆ መገበያየት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ አብዛኛው ግብይት እጅ በእጅ የሚፈፀም ስለሆነ ሁሉም ሰው ሳይዘናጋ የእጅ ንፅህናን መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ከፍተኛ ግብይት በሚፈፀምባቸው አካባቢዎች ላይ ህብረተሰቡ የጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉትን መልዕክቶች እየተገበረ እንዳልሆነ ለመገንዘብ  መቻላቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በአካባቢው ያስተዋሉት ቸልተኝነት የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስገድድ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ነጋዴው ማህበረሰብ የደንበኞቹን ጤንነት መጠበቅ ስላለበት በንግድ ልውውጥ ወቅት ርቀቱን ጠብቆ እንዲገበያይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ማከናወን አለበት ብለዋል።

በተጨማሪም በሽታው በአገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር የንግዱ ማህበረሰብ በምርቶች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባለማድረግና ምርቶችን ባለመደበቅ ይህን አስቸጋሪ ወቅት በትብብር ለማለፍ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

የተለያዩ ሚኒስትሮች ስለኮሮናቫይረስ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች በከተማዋ የተለያዩ አከባቢዎች በመዘዋወር የግንዛቤ የማስጨበጫ ስራ እያከናወኑ እንደሆነ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም