የሳምባ ምች ህመም ምልክቶች ታይቶበት ህይወቱ ያለፈ የ68 ዓመት ኢትዮጵያዊ የኮሮናቫይረስ እንደነበረበት እየተጣራ ነው

71

አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 23/2012( ኢዜአ) ከሳምባ ምች ህመም ምልክቶች ጋር በተያያዘ ህክም ሲደረግለት የነበረ የ68 ዓመት ኢትዮጵያዊ ዛሬ ህይወቱ ማለፉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

ግለሰቡ በኮሮናቫይረስ ስለመያዙ ለማጣራት ናሙና ተወስዶ ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነም ጠቁመዋል።።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ 68 የላብራቶሪ ምርመራ አካሄዷል።

በምርመራውም በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ ሶስት ሰዎች መኖራቸውን  መረጋገጡን ገልጸው፤  ሶስቱ ግለሰቦች ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ናቸው ብለዋል።

የመጀመሪያዋ ታማሚ የ33 አመት ሴት ስትሆን የጉዞ ታሪኳ ጅቡቲ፣ ብራዚል፣ ህንድ እና የመጨረሻ በረራዋ ኮንጎ ብራዛቪል መሆኑን ነው የተናገሩት።

ሁለተኛው ታማሚ የ 26 ዓመት ወንድ ሲሆን የስራ ባህሪው ከተለያዩ ተጓዥ መንገደኞች ጋር ግንኙነት ያለው ነው ተብሏል።

ሶስተኛው ታማሚ ደግሞ የ32 ዓመት ወንድ ሲሆን በበሽታው መያዙ ከተረጋገጠ ሰው ጋር ግንኙነት እንደነበረው ነው ዶክተር ሊያ የገለጹት።

ሶስቱም ታማሚዎች በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ሲሆን ከታማሚዎቹ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ሌሎች ሰዎች የመለየት ስራ እየተከናወነ እንደሆነም ሚኒስትሯ አውስተዋል።

በአሁኑ ሰዓት በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ያሉ 25 ታማሚዎች ሲኖሩ ሁለት ታማሚዎች በጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ሁለት ታማሚዎች ሙሉ በሙሉ አገግመው ለጥንቃቄ ሲባል በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

በለይቶ ማቆያ የነበረና ከሳምባ ምች ህመም ምልክቶች ጋር በተያያዘ ህክምና ሲደረግለት የነበረ የ68 ዓመት ኢትዮጵያዊ ዛሬ ህይወቱ ማለፉንም ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።

ህይወቱ ያለፈው ግለሰብ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ግንኙነት እንዳለው ለማረጋጋጥ ናሙና ተወስዶ የምርመራ ውጤቱ እየተጠበቀ መሆኑንም አብራርተው፤ የአስከሬን ምርመራም እየተከናወነ ነው ብለዋል።

መንግስት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ስራውን ለማስፋት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ሊያ ፤ በአሁኑ በአዲስ አበባ ሶስት የላብራቶሪ ምርመራ ማእከሎች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሎች በቅርብ ቀን የኮሮና ቫይረስ ምርምራ እንደሚጀመርም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የበሽታውን ስርጭት ግምት ውስጥ በማስገባት የመከላከያ መንገዶችን እና ከመንግስት ለሚተላለፉ እርምጃዎች ትኩረት በመስጠት እንዲተገብር ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም