ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ በመዘዋወር በኮሮናቫይረስ ዙሪያ የጥንቃቄ መልእክት አስተላልፈዋል

51

አዲስ አበባ፣መጋቢት 22/2012 (ኢዜአ) የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር በኮሮናቫይረስ ዙሪያ የጥንቃቄ ለኅብረተቡ መልእክት አስተላልፈዋል ፡፡

በዛሬው እለት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሒሩትን ጨምሮ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዲሁም ሌሎች በአዲስ አበባ በመዘዋወር የጥንቃቄ መልእክት አስተላልፈዋል።፣

ፕሮፌሰር ሒሩት በተለይ በጆሞና በኃይሌ ጋርመንት አካባቢ በመዘዋወር ባስተላለፉት መልዕክት ህብረተሰቡ አካላዊ ርቀትን እንዲጠብቅ  አሳስበዋል።

ቫይረሱ በአለም ዙሪያ በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ሒሩት ዜጎች ከመንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት የሚተላለፉ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

መዘናጋት ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል በመረዳት ሁሉም የራሱን፡ የቤተሰቦቹን ብሎም የሌሎችንም ደህንነት በመጠበቅ ሰብአዊና አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ መክረዋል።

የመንግስትና የህብረተሰቡ ቅንጅታዊ ስራ ከታከለበት ቫይረሱን የመከላከሉና የመቆጣጠሩ ስራ ቀላል መሆኑን በመጠቆም ለዚህም የእያንዳንዱ ግለሰብ ድርሻ ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ እስካሁን 25 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

እስካሁን በአለም ከ800 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሲያዙ ከ37 ሺህ 500 በላይ ሰዎችም ለህልፈት ተዳርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም