ሁዋጂያን ግሩፕ የተባለው የቻይና ኩባንያ ለትምህርት ሚኒስቴር 30 ሺህ የፊት ማስክ በስጦታ አበረከተ

52

አዲስ አበባ፣መጋቢት 22/2012 (ኢዜአ) ሀዋጂያን ግሩፕ የተባለው የቻይና ኩባንያ 30 ሺህ የፊትና አፍ መሸፈኛ ጭንብሎችን ለኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር በስጦታ አበረከተ።

የሁዋጂያን ግሩፕ ዳይሬክተር ዶክተር ግሬስ ዥንሁ በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል እየተደረገ ላለው ጥረት ኩባንያው የጀመረውን ድጋፍ አጠንክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ስጦታውን በመረከብ ለኩባንያው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የተገኘው ድጋፍ በዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በትምህርቱ ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት እንደሚከፋፈልም ገልጸዋል።

በአገሪቷ የተከሰተውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመግታት ሲባል የመማር ማስተማር ሂደቱ በመላ አገሪቱ እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወቃል።

በመሆኑም የበሽታውን ስርጭት መቀነስ እንዲቻል ቤተሰብ ልጆቹን ከቤት እንዳይወጡና በቤታቸው እንዲያጠኑ በማድረግ የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ ተጠይቋል።

በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ከ25 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችና ከ600 ሺህ በላይ መምህራን እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም