በደሴ ከተማና በሰሜን ወሎ ዞን ኮሮናን ለመከላከል የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ ።

42

ደሴ፣ወልዲያ፣መጋቢት 22/2012 (ኢዜአ) በደሴ ከተማና በሰሜን ወሎ ዞን ባለሃብቶችና ነዋሪዎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል 100 ሚሊዮን ብር የማሰባሰብ ስራ ጀምሯል ።

ከደሴ ከተማ ባለሃብቶች መካከል አቶ ኡመር ብርቁ ለኢዜአ አንደገለፁት የኮሮና ቫይረስን መከላከል ለመንግስት ብቻ ተገፍቶ የሚሰጥ አጀንዳ አይደለም።

አሁን ላይ በሃገሪቱ ብቻ ሳይሆን በአለም ላይ ስጋት የፈጠረ ተላላፊ በሽታ በመሆኑ ይህን ለመመከትና የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ተባብሮ መስራት ይገባል ብለዋል።

ባለሃብቱ አቅማቸው በፈቀደ መጠን በሽታውን መከላከል የሚያግዙ 50 የውሃ መያዣ ጎማ፤ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር፤ ሳሙናና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ቁሳቁሶች ከ50 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ሲሆን ቫይረሱ እስከሚጠፋ ድረስም ከመንግስት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላው የደሴ ጦሳ መድሃኒት ቤት አስተዳደርና ፋይናንስ ከፍል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ኃይሌ በበኩላቸው ለቫይረሱ መከላከያ የሚሆን የ100 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊትም የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ በማድረግ ከከተማ አስተዳደሩና ህብረተሰቡ ጎን መቆማቸውን ጠቁመው ከዚህ በኋላም የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በደሴ ከተማ የኮሮና መከላከል ኮማንድ ፖስት የህዝብ ግንኙት ኃላፊ አቶ ይልማ ተረፈ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ሊያደርስ የሚችለውን ችግር ለመቋቋም 100 ሚሊዮን ብር የማሰብሰብ ስራ ተጀምሯል፡፡

ገቢው የሚሰበሰበው ከህብረተሰቡ፣ ከባለሃብቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ከበጎ ፍቃደኞች እንደሆነ ገልፀዋል።

ባለፉት ሁለት ቀናት በተደረገ የማሰባሰብ እንቅስቃሴም ግማሽ ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል።

ከጥሬ ገንዘቡ በተጨማሪም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ ከ70 ካርቶን በላይ የተለያዩ ሳሙናዎች፣ 220 ኩንታል ጤፍ፣ ስንዴ፤ ቦለቄና ሌሎች የግብርና ምርቶች መሰበሰቡን ገልፀዋል።

በተጨማሪም 480 ሊትር ሳኒታይዘር በድጋፍ መገኘቱን ገልፀው ድጋፉን የማሰባሰብ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በተያያዘ ዜና በሰሜን ወሎ ዞን የኮሮና ቫይረስን ለመግታት የሚያግዝ ከ142ሺ ብር በላይ ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን የዞኑ የቀይ መስቀል ማህበር አስታውቋል ።

 የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ጸሐፊ አቶ ልዑልሰገድ ሲሳይ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስን መግታት እስከሚቻል ድረስ ማህበሩ ያለውን አቅም ሁሉ አሟጦ ድጋፍ ያደርጋል ።

ማህበሩ 210 ካርቶን ሳሙና፣ በረኪናና ሌሎች የንጽህ መስጫ ቁሳቁሶችን በዞኑ ለሚገኙ የወረዳ ጤና ተቋማት፣ ለተፈናቃዮችና ለማረሚያ ቤቶች አስረክቧል ።

በተጨማሪም የውሀ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ የጤና ተቋማትና ተፈናቃዮች 36 ጀሪካኖች መከፋፈላቸውን ጸሐፊው ተናግረዋል፡፡

በወልድያ መናኽሪያ በሮች ላይ ትልልቅ የውኃ ማጠራቀሚያ ታንከሮችን በማስቀመጥና አስፈላጊው የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በማሟላት ህብረተሰቡ እጁን እንዲታጠበ አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል ።

ከ100 በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሰልጠንም ህብረተሰቡን የማስተማርና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲሰጡ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት አያሌው እንደገለፁት የቀይ መስቀልን በጎ ተግባር ሌሎች ሊከተሉት ይገባል ።

ማህበሩ እስከ አሁን ድረስ ላደረገው ድጋፍ ኃላፊዋ አመስግነው ወደ ፊትም ችግሩ እየሰፋ ሊሄድ ስለሚችል አጠናክሮ እንዲቀጥልበት ጥሪ አቅርበዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም