በሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል የተባሉ በገንዘብ ተቀጡ

62

ሐረር ፣ መጋቢት 22 /2012 በሐረሪ ክልል በሸቀጦችና እህል ዋጋ ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል የተባሉ 25 ድርጅቶችና ግለሰቦች በገንዘብ መቀጣታቸውን የክልሉ ንግድ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ከሸቀጦች ጋር በተያያዘ የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር በሸማቾች ማህበራት በኩል ለህብረተሰቡ እያቀረበ መሆኑም ተገልጿል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ አብራሂም ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት በሐረር ከተማ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ከፖሊስ፣ጠቅላይ አቃቢ ህግ፣ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ጋር ግብረ ኃይል አቋቁመው እየሰሩ ነው።

በከተማው ባለፉት ሶስት ቀናት በምግብ ፣ ሸቀጦች፣ እህል፣ዘይትና በርበሬ ዋጋ ላይ ጭማሪ ያደረጉ 127 ድርጅቶች ግብረ ኃይሉ ማሸጉን አስረድተዋል።

ከነዚህም ውስጥ በተደጋጋሚ የቃል ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ተግባራዊ ባለማድረግ ለዋጋ ንረት መንገድ የከፈቱና ደንብ በጣሱ 25 ድርጅቶችና ግለሰቦች ከ2ሺህ እስከ 10ሺህ ብር መቀጣታቸውን አሰታውቀዋል።

የምግብ ዘይት ባለአምስት ሊትር 300 ብር በነበረው ዋጋ ላይ እስከ 150 ብር ፣ ስኳር  ኪሎው 32 ብር የሆነው በእጥፍ ያህል መጨመር እንዲሁም እንዲዘጉ ገደብ የተጣለባቸው መጠጥ  ቤቶች   ከፍተው ሲሸጡ መገኘታቸው ለቅጣቱ የተጠቀሱባቸው ጥፋቶች ናቸው።

ከቅጣቱ የተገኘው ከ100ሺ ብር በላይ  ለመንግስት  ገቢ መደረጉን ኃላፊው አመልክተዋል።

ከዚህም ሌላ 17 ግለሰቦችና ድርጅቶች ደግሞ ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በህግ እየታየ እንደሚገኝ ጠቁመው ቀሪዎቹ ደግሞ በመጨረሻ  ማስጠንቀቂያ  መታለፋቸውን ተናግረዋል።

እንደ አቶ አብዱልፈታህ ገለጻ የሸቀጦች አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር ቢሮው በሸማቾች ማህበራት በኩል የምግብ ዘይትና ስኳር  ለህብረተሰቡ እያቀረበ ይገኛል።

እስካሁንም በክልሉ ለሚገኙ 43 የሸማቾች ማህበራት በመንግስት በኩል የተገኘ 8ሺህ ካርቶን ዘይትና  450 ኩንታል ስኳር በማከፋፈል ለህብረተሰቡ እንዲደርስ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

5ሺህ ኩንታል የስንዴ ዱቄት ደግሞ ወደ ክልሉ እየገባ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በተጨማሪ በክልሉ ለሚገኙ የህጻናት ማሳደጊያና አረጋውያን መርጃ ማዕከላትም ምግብ ነክ ፍጆታዎች እንደሚከፋፈል አስታውቀዋል።

የሐረሪ ክልል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ከኮረና ቫይረስ ጋር በተያያዘ መንግስት የሚያወጣውን ምክረ ሃሳብና መመሪያዎች ተግባራዊ በማያደርጉት  ላይ እርምጃ እንደሚወስድ መግለጹ ይታሻል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም