የኡለማዎች ምክር ቤት የኮሮና ስርጭትን ለመግታት የጁማአና ጀማአ ሶላትላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም ወሰነ

76

አዲስ አበባ መጋቢት 22/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የኡለማዎች ምክር ቤት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሲባል የጁማአ እና ጀማዓ ሶላት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም ወሰነ።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ ባለፈው መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ያስችላል ያላቸውን ባለ 4 ነጥብ ያለው መመሪያ ማስተላለፉ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየሰፋ በመምጣቱ ሌላ ተጨማሪ ሃይማኖታዊ ብያኔ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ተጨማሪ ነጥቦችን አካቶ ውሳኔ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ዐሀፊ ሼህ ቃሲም መሀመድ ታጁዲን በዑላማዎች ምክር ቤት የተላለፈውን ውሳኔ በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህ መሰረትም ከዛሬ ጀምሮ በሽታው በሰው ልጆች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት መቆሙ በጤና ባለሙያዎች እስኪ ረጋገጥ ድረሰ ዘወትር አርብ የሚካሄደው የጁማዓ እና የጀማአ (የጋራ) ሶላት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም የዑለማዎች ምክር ቤት ወስኗል።

ውሳኔው የተላለፈው የወረርሽኙ መስፋፋትና አደገኛነት አስጊ መሆኑን ተከትሎ መሆኑም ታውቋል።

በመሆኑም ሁሉም የሙስሊሙ ማህበረሰብ በቤቱ በመሆን መስገድ እንዳለበት ሼህ ቃሲም መሀመድ አሳስበዋል።

የጤና ተቋማትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የሚያወጧቸውን መመሪያዎች እና የሚሰጧቸውን የጥንቃቄ የመከላከያ አቅጣጫዎች መቀበል እና በስራ ላይ ማዋል ሀይማኖታዊ ግዴታ መሆኑንም አስረድተዋል።

በገጠርም ሆነ በከተማ በስብስብ መልክ ሀይማኖታዊ ትምህርት መስጠት ለበሽታው ስርጭት ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ተወስኗል።

የበሽታው ስርጭት እንዳይኖር ለማድረግ በእጅ ሰላምታ መለዋወጥ መቅረት እንዳለበትም ተጠቁሟል።

በተያያዘ ዜና በጠቅላይ ምክር ቤቱ የተቋቋመው የመጅሊስ ኮሮናቫይረስ አደጋ መከላከል አብይ ግብር ሀይል የእስልምና ትምህርት ቤቶችን ለለይቶ ማቆያ አገልግሎት እንዲውሉ በጊዜያዊነት መለግሱን አስታውቋል።

በዚህ መሰረት የአወሊያ፣ የነሰር እና በኦሮሚያ ክልል የሚገኘውን የወሊሶ ማዕከል ለዜጎች የለይቶ ማቆያ እና የህክምና መስጫ ሆኖ እንዲያገለግል ለሚመለከተው የመንግስት አካል በጊዜያዊነት ማስረከባቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም