የጋራ ምክር ቤቱ በግድቡ ላይ በጣልቃ ገብነት የሚደረግ ድርድር መኖር የለበትም አለ

84

አዲስ አበባ መጋቢት 22/2012(ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሌሎች ጣልቃ ገብነት የሚደረግ ድርድር መኖር የለበትም ሲል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአሜሪካ ድርድር ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ለጊዜው በድርድሩ መሳተፍ አልችልም የሚል አቋም ብታንጸባርቅም አሜሪካና የዓለም ባንክ ከታዛቢነት ሚናቸው ባለፈ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር መሞከራቸው ተገልጿል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር ፖሊሲ ቀርፃለች።

ማንኛውም ፓርቲ ወይም ኢትዮጵያዊ በአባይ ወንዝና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ተመሳሳይ እሳቤና አረዳድ አላቸው ብለዋል።

በመሆኑም በፖለቲካ ፓርቲዎች ብሎም በሌሎች አካላት መካከል ልዩነት ቢኖርም በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ግን ልዩነት መፍጠር እንደማይቻል ገልጸዋል።

"በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለውን የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ልዩነት እንደ ውስጣዊ ክፍፍል የሚቆጥሩ አካላትም አይሳካላቸውም፤ አርፈው ይቀመጡ" ብለዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን መገንባት ፍትሃዊ የውሃ ሃብቱን የመጠቀም ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የአገር ሉዓላዊነትና የክብር ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ በሌሎች ጣልቃ ገብነት የሚደረግ ድርድር እንዲኖር መፍቀድ የለባትም ብለዋል።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ሶስቱ ተደራድረው ውሃውን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መጠቀም፤ ሶስቱ መስማማት ካልቻሉ ሌሎች አፍሪካዊያን ቢያሸማግሉ ይሻላል ነው ያሉት።

"አባይና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በችግር ውስጥ ሆነንም ወደጎን የማንተወው የሉዓላዊነታች መገለጫ፤ የቀጣይ የትውልድ አሻራችን ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም