በአዲስ አበባ የቤንዚን እጥርት ተከስቷል--የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት

95

አዲስ አበባ፣መጋቢት 22/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የቤንዚን እጥርት ተከስቶ ማህበራዊ ችግር እያሰከተለ ነው።

የቤንዚን እጥረቱ ያጋጠመው በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሱዳን ድንበሯን በመዝጋቷ መሆኑን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ገልጿል።

የኢዜአ ሪፖርተር በአዲስ አበባ በሚገኙ አንዳንድ የነዳጅ ማደያዎች ተዘዋውሮ ባደረገው ቅኝት በቤንዚን እጥረት ሳቢያ በርካታ ተሽከርካሪዎች ተሰልፈው አስተውሏል፡፡

የቤንዚን እጥረቱን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለማርያምን ኢዜአ በስልክ አነጋግሯል፡፡

ኢትዮጵያ ነዳጅ የምታስገባባቸው አገሮቹ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ በድንበር አካባቢ የትራንስፓርት እንቅስቃሴ ዝግ በማድረጋቸው እጥረቱ መከሰቱን ገልፀዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ የቤንዚን ፍጆታ 50 በመቶ የሚሆነው የሚገባው ከሱዳን መሆኑ ይነገራል።

በዚህም ካርቱም ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሱዳን መንግስት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውይይት አድርጓል።

በተደረገው ውይይትም 15 የሚሆኑ የቤንዚን ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ወደ ሱዳን ለመግባት መተማ አካባቢ መድረሳቸውን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለማርያም ገልጸዋል።

ጅቡቲ በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ ምክንያት ድንበሯን ብትዘጋም ኢትዮጵያ በጅቡቲ በኩል ነዳጅ በልዩ ሁኔታ እንድታስገባ እየተደረገ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።  

ሆኖም በጅቡቲ በኩል የሚገባው ቤንዚን አገሪቱ የሚያስፈልጋትን ፍጆታ ማሟላት እንደማይችል አስረድተዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ከሆነ አሁን የተፈጠረው ጊዜያዊ የቤንዚን እጥረት በሚቀጥለው ሳምንት ሙሉ ለሙሉ ይወገዳለ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም