በጋምቤላ ክልል ኮሮናን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው

60

መጋቢት 22/2012 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥረት በመደገፍ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ጥሪ አቀረቡ ።

ቫይረሱን ለመከላከል የሚተላለፉ መመሪያዎችን ተግባራዊ በማያደርጉ አካላት ላይ የክልሉ መንግስት ህጋዊ እርምጃ  እንደሚወስድም አስታውቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለኢዜአ እንደገለጹት ቫይረሱ በሀገሪቱ መከሰቱ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ የተለያዩ ግብረ ኃይሎች ተቋቁመው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

"ክልሉ ሰፊ የድንበር ወሰንና ከፍተኛ የስደተኛ ቁጥር ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን ችግር ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተሰራ ነው "ብለዋል።

እንደ ሀገር በተላለፈው መመሪያ መሰረትም ስምንት የክልሉ ጠረፋ የመግቢያና የመውጫ በሮች እንዲዘጉ መደረጉን  ተናግረዋል።

አቶ ኡሞድ እንዳሉት በክልሉ የሚገኙ ስደተኞችም ከመጠለያ ጣቢያ ውጪ የሚያደርጉት ልቅ እንቅስቃሴ ላለተወሰነ ጊዜ እንዲገደብ  ተደርጓል።

በቫይረሱ የተጠረጠሩ ሰዎች ለይቶ ማቆያ ሰባት ቦታዎች ተለይተው በባለሙያና በህክምና ቁሳቁስ ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ቫይረሱን ለመከላከል የሚተላለፉ መመሪያዎችን መሰረት በማድረግም የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግም እንዲሁ።  

ሆኖም በአንዳንድ የመጠጥ፣ ጫት፣ ሻይ ቤቶችና የእምነት ተቋማት አካባቢ ቫይረሱን ለመከላከል የሚተላለፉ መመሪያዎችን ተግባራዊ ያለማድረግ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

"ለህብረተሰቡ ጤና ሲባል በመንግስት የሚተላለፉ መመሪያዎችን በማይተገብሩ አካላት ላይ የክልሉ መንግስት ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ ይሆናል" ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ለጀመራቸው ስራዎች መሳካት ህዝብ የሚተላለፉ መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ እራሱን ከቫይረሱ ለመጠበቅ ጠንክሮ እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

በተመሳሳይ  በድሬዳዋ አስተዳደር አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት ነዋሪዎች መካከል የማህበራዊ ሣይንስ  ባለሙያ አቶ ዘመድሁን ተስፋሁን እንዳሉት ፤ የመንግስት  እርምጃዎች ጃ ፍሬያማ የሚሆኑት ሁሉም ነዋሪ ከንክኪ በመቆጠብና ርቀቱን ጠብቆ ህይወቱን ሲመራ ብቻ ነው።

በአስተዳደሩ  ቀፊራ፣ሩዝ ተራ፣አሸዋ የሚባሉ ገበያ አካባቢዎች የሚስተዋለው ግድየለሽነት ተገቢነት እንደሌለውና ሊስተካከል እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በከተማው አንዳንድ አካባቢዎች ቫይረሱን ለመከላከል ነዋሪውና ተቋማት የሚያደርጉት ጥንቃቄና መመሪያዎችን የመተግበር ልማድ አበረታች እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የማበረሰብ ጤና ባለሙያው አቶ ባህሩዲን ሸሪፍ ናቸው።

"ሁሉንም ነገር በፈጣሪና በመንግስት ላይ መተው ሣይሆን፤ በተሰጠን አእምሮ የመከላከያ መንገዶችን በየቀኑ መተግበር አለብን፤ ከተቻለ እቤት መቀመጥ ይገባናል "ብለዋል፡፡

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ መስፍን ለማ  በበኩላቸው በዚህ ክፉ ወቅት ባለሃብቱና ምሁሩ የቫይረሱን ስርጭት የመከላከል ዘመቻውን ለማሳካት መረባረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የድሬዳዋ አብዛኛው ማህበረሰብ በዕለት ንግድና በአገልግሎት ዘርፍ ላይ ህይወቱን የመሰረተ በመሆኑ ገበያዎችን በአንድ ጊዜ ከመዝጋት ይልቅ በተደጋጋሚ ጊዜ ማስተማርና መቆጣጠር  ብሶ ከመጣ ደግሞ ህይወትን የማዳን እርምጃ ይቀድማል ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም