በማእከላዊ ጎንደር በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ምርት ተወረሰ

56

ጎንደር ፣ሆሳእና መጋቢት 22/2012 (ኢዜአ) በማእከላዊ ጎንደር ዞን በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ የ17 ነጋዴዎች  ምርት ሲወረስ በሃዲያ ዞን ደግሞ ህገ ወጥ የቤንዚን ንግድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ ።

 የማእከላዊ ጎንደር ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አይቸው ታረቀኝ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የኮሮና ቫይረስ በሽታን ምክንያት በማድረግ በዞኑ የዋጋ ንረትና የምርት እጥረት ለመፍጠር ሙከራ ያደረጉ 17 ነጋዴዎች ንብረታቸው እንዲወረስ ተደርጓል፡፡

ነጋዴዎቹ ቤንዚን፤ ነጭ ጋዝ፣ ናፍጣና የሞተር ዘይቶችን ደብቆ በማከማቸትና ከ650 ሊትር በላይ የምግብ ዘይት፤ 12 ኩንታል በርበሬና 10 ኩንታል ስኳር በህገ-ወጥ መንገድ ሲያጓጉዙ የተገኙ ናቸው፡፡

በዞኑ የተቋቋመው ግብረሃይል ለተከታታይ 15 ቀናት በአራት ወረዳዎች ባደረገው ቁጥጥርና ክትትል  ነጋዴዎቹ በመጋዘን ደብቀው በማከማቸትና ከተፈቀደ አካባቢ ውጪ ሲያጓጉዙ በመገኘታቸው እርምጃው ተወስዷል።

በሌላም በኩል በዞኑ 15 ወረዳዎች በሽታውን ምክንያት በማድረግ በፍጆታ ምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 367 የንግድ ድርጅቶች ላይ ግብረ ሃይሉ እርምጃ መወሰዱን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

በንግድ ህጉ መሰረት ህግ ተላልፈው ከተገኙ 350 የንግድ ድርጅቶች መካከል አብዛኛዎቹ በማስጠንቀቂያ እንዲታለፉ ፣ ከፊሎቹ እንዲታሸጉና የተወሰኑት ደግሞ ንግድ ፈቃዳቸው እንዲወረስ ተደርጓል ።

17 የንግድ ድርጅት ባለቤቶች ደግሞ በህግ-ቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

የንግድ ድርጅቶቹ በግብርናና በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ከሶስት እጥፍ በላይ ምክንታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ በሸማቹ ህብረተሰብ ላይ የኑሮ ውድነት በመፍጠር ህገ ወጥ የንግድ ተግባር የፈጸሙ ናቸው፡፡

በማእከላዊ ጎንደር ዞን ህጋዊ  የንግድ ፈቃድ አውጥተው የሚሰሩ 20 ሺህ የሚጠጉ ህጋዊ ነጋዴዎች እንደሚገኙ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡  

 በሌላ በኩል ደግሞ በሃዲያ ዞን ህገ ወጥ የቤንዚን ንግድ በመስፋፋቱ ለብዝበዛ መዳረጋቸውን የታክሲ አሽከርካሪዎችና ተገልጋዮች ቅሬታቸውን ገለፀዋል ።

የሃድያ ዞን ንግድና ገቢያ ልማት መምሪያ በበኩሉ በቅንጅት ጉድለት የታዩ ችግሮችን በማስተካከል መፍትሄ ለማምጣት እንደሚሰራ አስታውቋል።

በሃዲያ ዞን የሆሳዕና ከተማ ባጃጅ አሽከርካሪ ወጣት ሄኖክ ካሳ እንደሚለው በዚህ ዓመት በነዳጅ ማደያዎች የሚስተዋሉ የአቅርቦት ችግሮች መፍትሄ ባለመስጠቱ አንድ ሊትር ቤንዚን በ45 ብር ለመግዛት መገደዱን ተነግሯል ።

በአቅርቦቱ ላይ ለሚስተዋለው መሰረታዊ ችግር መንስኤው የነዳጅ ማደያዎች በመደበኛ ከሚሸጡበት ዋጋ ጭማሪ በማድረግ ለጥቁር ገበያ ቸርቻሪዎች አሳልፈው ስለሚሸጡ መሆኑን ይናገራል።

ተቆጣጣሪው አካል ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠቱ ማደያዎች ቤንዚን ቢያስገቡም ትንሽ ከቀዱ በኋላ እንዳለቀ በማስመሰል ዘግተው በጄሪካን እንደሚሸጡ ጠቁሟል።

በከተማው ህገ ወጥ የቤንዚል ንግድን ለመከላከል በመንገድ ላይ በሚሸጡትም ሆነ በማደያዎች ላይ ተገቢ ቁጥጥር ባለመደረጉ ህገ ወጥነት እንዲንሰራፋ ማድረጉን ጠቁሞ መንግስት መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቋል።

“በከተማዋ የሚገኙ ማደያዎች የሚጠበቅባቸውን ያክል አገልግሎት ባለመስጠታቸው በህገ ወጥ ነጋዴዎች እየተበዘበዝን ነው”ያሉት ደግሞ ሌላኛው የባጃጅ አሽከርካሪ አቶ ሲሳይ ሞሊቶ ናቸው።

አንድ ሊትር ቤንዚን በውድ ዋጋ ገዝተው አገልግሎት በመስጠት ተጠቃሚ መሆን ባለመቻላቸው ቤተሰባቸውን ማስተዳደር እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

በዞኑ ሌሞ ወረዳ ጀዌ ቀበሌ ነዋሪና ሞተር ሳይክል በማከራየት ቤተሰባቸውን እንደሚያስተዳድሩ የገለጹት አቶ አዳነ መኒቶ በበኩላቸው የቤንዚን እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ በስራቸው ላይ ተፅዕኖ እያደረሰባቸው ይገኛል።

ህገ ወጥ ነጋዴዎቹ እንደፈለጉት ዋጋውን ከማናር ባለፈ ውሃ ደባልቀው ስለሚሸጡ ንብረታቸው ለብልሽት እየተዳረገ መቸገራቸውን ተናግረዋል።

የሀድያ ዞን ንግድና ገቢያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ዶክተር አዮብ በቀለ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በዞኑ ሰባት የቤንዚን ማደያዎች አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ተደራሽ ባለመሆናቸው  እጥረት መፈጠሩን ገልጸዋል።

ያሉትም ውስን ማደያዎች ህብረተሰቡን ከማገልገል ይልቅ ጨለማን ተገን በማድረግ መመሪያው ከሚያዘው ውጪ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በመሻት በህገወጥ መንገድ እንደሚሸጡ ተረጋግጧል ብለዋል።

የተገኘውን መረጃ መነሻ በማድረግ አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁና ችግሩን በዘለቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ከመምሪያ ኃላፊው ገለፃ ለመረዳት ተችሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም