የለውጡን ጉዞ ሊያሰናክሉ የሚጥሩትን ህዝቡ አንድነቱን በማጠናከር ሊታገላቸው ይገባል... አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

63
ባህር ዳር ሰኔ 24/2010  “ዛሬ አገሪቱ ደስታና ፍቅር የሚታይባት አገር ብቻ ሳትሆን የህዝቡ አንድ መሆን የእግር እሳት የሆነባቸው የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች የለውጡን ጉዞ ሊያሰናክሉ እየሰሩ በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት” ሲሉ የአማራ ክልለ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሳሰቡ። ርዕሰ መስተዳደሩ ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ላመጡት አገራዊ መግባባትና የመተባባር መንፈስ ድጋፍ ለመስጠት በባህር ዳር ከተማ  በተካሄደው ሰልፍ ላይ ለታደመው  ህዝብ ባደረጉት ንግግር ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ፍቅር እርቦት፣ አንድነትና መተባበር ጠፍቶበት የቆየ መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ህዝቡ በከፈለው መስዋትነት በአገሪቱ የፍቅር፣ የአንድነትና የመተሳሰብ መንፈስ በመላ አገሪቱ እየጎለበተ መሆኑን ገልጸዋል። በአገሪቱ ፍታዊ አሰራርና ህዝቡ በተደጋጋሚ ሲያነሳቸውና ሲፈልጋቸው የነበሩ የመልካም አስተዳደር ስራዎችም መልስ መስጠት እንደጀመሩ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ የህዝቡን አንድ መሆን የማይሹ፣ ሰላምና መተባበር ጠላታቸው የሆነና ዛሬም የራሳቸውን ፍላጎት ለማራመድ የሚጥሩ አካላት የተፈጠረውን አገራዊ ፍቅር ለማጠልሸት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አስረድተዋል። የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና አገሪቱ ወደ ነበረችበት ገናናነቷ እንድትመለስ ህዝቡ  አንድነትንና የአገሪቱን ሰላም የማይፈልጉ አካላትን የመታገል ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል። ዛሬ የተጀመረው ለውጥና አገራዊ አንድነት እንዲመጣ ወጣቱ የከፈለው ከፍተኛ መስዋትነት መሰረት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው። መንግስት ህዝቡ ሲፈልግ የነበረውን የመልካም አስተዳደርና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለመካስ በአዲስ መንፈስ ሥራ መጀመሩን አመልክተዋል። "በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየነፈሰ ላለው የፍቅር አየር ህዝቡ በተለይም ወጣቱ መሰረት እንደሆነ ሁሉ ወደፊትም የሚኖረውን ማናቸውም ጥያቄ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማንሳት ይኖርበታል" ብለዋል። መንግስት ችግሮችን እያዳመጠ ከስህተቱ እየታረመ ሥራዎችን ለመስራት ቆርጦ የተነሳ በመሆኑ ወጣቱ አሁን የጀመርውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመደገፍ በባህር ዳር ከተማ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ዛሬ በተዘጋጀው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከከተማዋ ነዋሪዎች በተጨማሪ ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የለውጡ ደጋፊዎች መሳተፋቸውንና ሰልፉም በሰላም መጠናቀቁ ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም