የንግዱ ማህበረሰብ ከመቸውም ጊዜ በላይ አሁን ላይ ከህዝብ ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀረበ

63

አዲስ አበባ፣መጋቢት 22/2012 (ኢዜአ) የንግዱ ማህበረሰብ አሁን ያለውን ክፉ ጊዜ ለማለፍ ከመቸውም ጊዜ በላይ አሁን ላይ ከህዝብ ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀረበ።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር በመተባበር ከተለያዩ አስመጪዎች፣ አምራቾችና አከፋፋዮች ጋር እየተወያየ ነው።

የውይይቱ ዋነኛ ዓላማም የኮረናቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ በፍላጐትና አቅርቦት ላይ  እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መሆኑ ተገልጿል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በዓለም ላይ በወረርሽኝ መልክ እየተሰራጨ ያለው የኮሮናቫይረስ በዓለም ላይ እያስከተለ ካለው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ባሻገር በሰዎች ጤና ላይም ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በኢትዮጵያ በነፃ ምርትና አገልግሎት እያቀረቡ ያሉ ዜጎች እንዳሉ ሁሉ የቫይረሱን መከሰት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በምርትና አገልግሎት ላይ ዋጋ የሚጨምሩ መኖራቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም የንግዱ ማህበረሰብ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከንግድና ከሚያገኘው ትርፉ በላይ ዜጎችን ስለማገዝ፣ የሰዎችን ህይወት ስለማቆየት ቅድሚያ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ  ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ በበኩላቸው በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ በሽታውን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከራስ በላይ ለሌሎች አለማሰብ አግባብ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ከመነሻው የዋጋ መጨመር ችግር ሳይኖር በሰው ሰራሽ ችግሮች አስመጪዎች፣ አከፋፋዮችና አምራቾች ምርትን በመገደብ፣ በማከማቸትና በመደበቅ የተፈጠረው ችግር በአቅርቦት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ወቅት ምርትን በነፃና በቅናሽ በማቅረብ እንዲሁም ምክንያት አልባ የዋጋ ጭማሪን በማስወገድ የንግዱ ማህበረሰብ ከህዝብ ጎን በመቆም ማህበራዊ ኃላፊነቱንና ወገንተኝነቱንም እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም