በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 25 ደርሷል

46

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ 66 የላብራቶሪ ምርመራ አካሄዶ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ ሶስት ሰዎች መገኘታቸውን ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሰረት በአጠቃላይ በሀገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሃያ አምስት (25) ደርሷል፡፡

በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት ሁለት ግለሰቦች የ30 ዓመትና የ36 ዓመት ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ በተመሳሳይ በረራ ከዱባይ በመጋቢት 15 /2012 ዓ.ም ወደ ሀገር የገቡ ናቸው።

ሁለቱም ሰዎች ወደ ሀገር ከገቡ በኋላ በአስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ሲሆን የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው በተደረገላቸው የላብራቶሪ ምርመራ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡ ነው የተጠቀሰው።

ሶስተኛዋ ታማሚ የ60 ዓመት እድሜ ያላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ መጋቢት 6/2012 ዓ.ም ከፈረንሳይ የተመለሱና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቶ የበሽታውን ምልክት በማሳየታቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው በተደረገላቸው የላብራቶሪ ምርመራ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ሶስቱም ታማሚዎች በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሆነም ተገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ያሉ ሃያ አንድ (21) ታማሚዎች ሲኖሩ ሁለት ታማሚዎች በጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ ተጠቅሷል።

ከዚህ በፊት እንደተገለጸው ሁለት ታማሚዎች ወደ ሀገራቸውመመለሳቸው እና ሁለት ታማሚዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ያገገሙ ሲሆን ለጥንቃቄ ሲባል በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ነው ጤና ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ የገለጸው።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይህ መረጃ እስከ ተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ በአጠቃላይ 1013 የላቦራቶሪ ምርመራ ማድረጉም ተገልጿል።

ህብረተሰቡ የበሽታውን ስርጭት ግምት ውስጥ በማስገባት የመከላከያ መንገዶችን እና ከመንግስት የሚተላለፉ እርምጃዎችን ትኩረት በመስጠት እንዲተገበር ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም