ከ15 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃ በቁጥጥር ስር ዋለ

87

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2012( ኢዜአ) ባለፉት 5 ቀናት በሀገሪቱ  በተለያዩ ጉምሩክ ኬላ ጣብያዎች 15 ሚሊየን 753 ሺህ 147 ብር የሚገመት የተለያዩ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ።


ከነዚህም መካከል ለተከታተይ 3 ቀናት ክትትል ሲደረግባቸው የነበሩ በእግር በጫካ ውስጥ ወደ ጂቡቲ ይነዱ የነበሩ ግምታዊ ዋጋቸው ከ2,368,000 ብር በላይ የሆነ 296 እንስሳት ከድሬደዋ በግምት ከ220 ኪ.ሜ ርቀት ድንበር  በድሬደዋ ጉምሩክ ሠራተኞችና በፌደራል ፖሊስ አባላት አማካኝነት በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ እቃዎች በህገ ወጥ መንገድ በመኪና ተጭኖ ሲገባ በተደረገ ቁጥጥር የተለየ ሲሆን እቃው ተጨማሪ ፍተሻ ሲደረግበት 1 ሽህ 541 የክላሽ ጥይቶች በድሬደዋ ጉምሩክ ሠራተኞች ተይዘዋል፡፡


በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የገባ ሰንፍላሆር ዘይት የጉምሩክ ስነ ስርዓት ተፈጽሞበት ከተለቀቀ በኋላ ዳግም ድንገተኛ ፍተሻ የዋጋ ልዩነት መኖሩን ስለ ተረጋገጠ አስመጪ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር ተጨማሪ እንዲከፍል ተደርጓል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች የኮንትሮባንድ ዕቃዎች  በጅግጅጋ ፤ ሞያሌ ፤ ገናሌ፤አዳማ፤ አዋሽ ፤ ሀዋሳ ፤ እና ሌሎች የጉምሩክ ኬላ ጣብያዎች ላይ የተያዙ ሲሆን የኮንትሮባንድ እቃዎቹም የተለያዩ የአዋቂዎችና ህፃናት አልባሳት ፤ ኤሌክትሮኒክስ፤ጊዜው ያለፈባቸው ምግቦችና መጠጦች ፤ ዘይት እና የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃ ዓይነቶች ናቸው ።


በመሆኑም ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ በሀገርና በህዝብ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ችግር እንደሚያስከትል በመረዳት ሁሉም ከመንግስት ጎን በመቆም በተባበረ ክንድ ለችግሩ መፍትሄ መሆን እንዳለበት የገቢዎች ሚኒስቴር ሀገራዊ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ (የገቢዎች ሚኒስቴር)

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም