የኮሮናቫይረስን ለመከላከል መዘናጋት አይገባም … የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮናቫይረስን ለመከላከል መዘናጋት አይገባም … የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር
ባህር ዳር፤መጋቢት 21/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ህዝቡ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አላስፈላጊ ጭንቀትና መዘናጋትን በመተው በተገቢው ጥንቃቄ ከቫይረሱ እራሱን እንዲጠብቅ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ አሳሰቡ።
በክልሉ የኮሮና ቫይረስን የመከላከል ሒደት ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ ማምሻውን መግለጫ ተሰጥቷል።
ምክትል ርዕስ መስተዳደሩ በመግለጫው እንዳሉት የክልሉ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ሊያደርስ የሚችለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከግምት በማስገባት አስፈላጊውን ሁሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ ነው።
ቫይረሱ በክልሉ ውስጥ መከሰቱን ጠቅሰው ህዝቡ አላስፈላጊ ጭንቀትና ሽብር ውስጥ ሳይገባ እስከ አሁን ምንም አይነት መድሃኒት ያልተገኘለትን በሽታ በጥንቃቄ መከላከል እንዳለበት አሳስበዋል።
በተለይም በመንግስትና በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ መመሪያዎችና ሳይንሳዊ የመከላከያ መንገዶች ሳይሸራርፉ መተግበር የግድ እንደሆነም ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ገልፀዋል።
“ይህ ወቅት ለሃገራችንም ሆነ ለክልላችን ህዝቦች አስቸጋሪ ወቅት ነው” ያሉት ዶክተር ፈንታ በትብብርና በታላቅ ትጋት በመወጣት ሃገራዊ ጀግንነትን መላበስ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በክልሉ ባለፉት ሳምንታት በቫይረሱ የተጠረጠሩ 27 ሰዎች ተለይተው ክትትል ሲደረግላቸው መቆየቱን አመልክተው፤ “ከእነዚሁህ ውስጥ ሁለቱ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ዛሬ ተረጋግጧል”ብለዋል።
በባህርዳርና አዊ ዞን ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረጋገጡት ጋር ንክኪ የነበራቸው 24 ሰዎችን በለይቶ ማቆያ በማስገባት ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነም አስታውቀዋል።
የክልሉ መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከነገ ጀምሮ ከናፍጣና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ከሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች በስተቀር የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከየትኛውም አቅጣጫ እንዳይገቡ መወሰኑንም ተናግረዋል።
ህዝቡ የሚወጡ መመሪያዎችን በአግባቡ መተግበር ካልቻለና ችግሩ ከዚህ በላይ እየከፋ የሚሄድ ከሆነም በክልሉ ውስጥም ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረጉ ጉዞዎች ሊዘጉ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።
ጉዳዩን በየጊዜው በመገምገም ችግሩ ከፍ ካለም ከቤት ያለመውጣት እገዳዎች ጭምር ሊተላለፉ እንደሚችሉ ጠቅሰው፤ ይህ ከመሆኑ በፊት ህብረተሰቡ እራሱን ከቫይረሱ ሊከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል።
አጅን በተገቢው ሁኔታ ከመታጠብ ጀምሮ የእጅ ሰላምታን አለማድረግና ማህበራዊ መገፋፋትን ማቆም ከተቻለ በሽታውን 60 በመቶ መቆጣጠር እንደሚቻል የገለጹት ደግሞ የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ናቸው።
እራስን ከበሽታው ለማዳን ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ መመሪያዎች ትኩረት ባለመሰጠቱ በችግሩ አሳሳቢነት ልክ እየተተገበረ አለመሆኑን ጠቁመው “ህብረተሰቡ ሊነቃና የሚነገረውን የመከላከያ ዘዴ በሃላፊነት ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል”ብለዋል።
“ሃሰተኛና አደናጋሪ መረጃዎችን ለመጠበቅም የኮሮና ቫይረስን በተመለከተ የየዕለቱ መረጃ እንዲደርስ ይደረጋል” ያሉት ደግሞ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይርሳው ናቸው።
በመሆኑም ህዝቡ የመንግስትን መረጃ ሳይጠራጠር በመከታተል እራሱን ከቫይረሱ መጠበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።