የኢጋድ አባል አገሮች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቀናጀ ቀጠናዊ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ስርአት ለመዘርጋት ተስማሙ

75

መጋቢት 21/2012 የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አባል አገሮች የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል የተቀናጀ ቀጠናዊ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ስርአት ለመዘርጋት ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ።

አባል አገሮቹ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰዋል።

የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን መሪዎች በቀጠናው የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚወሰዱ እርምጃዎችና ፈተዎችን ላይ ለመምከር ዛሬ የቴሌኮንፈረስ ውይይት አድርገዋል።

የአባል አገሮቹ መሪዎች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቀናጀ ቀጠናዊ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ስርአት ለመዘርጋት መስማማታቸው ተገልጿል።

መሪዎቹ ስርአቱን የመዘርጋት ሃላፊነት ለኢጋድ ጽህፈት ቤት መስጠታቸውን ኢጋድ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በተጨማሪም ጽህፈት ቤቱ ለኮሮናቫይረስ የተቀናጀ ምላሽ መስጠት እንዲቻል መሪዎቹ የሚወያዩባቸው መርሃግብሮች እንዲያዘጋጅ ሃላፊነት ተሰጥቶታል።

የኢጋድ አባል አገሮች ኮቪድ-19 አስመልክቶ በቫይረሱ የተጠቁና የተጠረጠ ሰዎችን ጨምሮ በቀጠናው ያለውን የመረጃ ልውውጥ ለማጠናከር መስማማታቸውን ገልጿል።

መሪዎቹ የተቀናጀ የድንበር ቁጥጥርና አስተዳደር እንዲኖርና የጭነት እቃዎች በቅልጥፍና እንዲጓጓዙ ለማድረግ በየአገራቱ ድንበርን አስመልክቶ የሚሰሩ ተቋማት በትብብር እንዲሰሩ መመሪያ ለመስጠት መስማማታቸውም ተጠቅሷል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢጋድ አገሮች ውስጥ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ለስደተኞች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም በቀጠናው ያሉ የሰብአዊ እርዳታ መተላለፊያዎች ክፍት ሆነው አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረጉ ያለውን ጥረት ዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ እንዲደግፍ ጠይቀዋል።

የኢጋድ አባል አገሮች ከዓለም አቀፍ ተቋማትና አጋሮች ቫይረሱን አስመልክቶ የሚደረጉ የፋይናንስ ድጋፎችን በጋራ ለመጠቀም ተስማምተዋል።

የኢጋድ ቀጠና የኮሮናቫይረስ ሊያደርስ የሚችለውን ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለመቀነስ ገንዘብና የተለያዩ ሀብቶች እንደሚያስፈልጉት ያመለከተው መግለጫው፤ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ እያደረገ ያለውን ድጋፍና አስተዋጽኦ እንዲያሳድግ ጥሪ አቅርቧል።

የኮሮናቫይረስ በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የአባል አገሮች የፋይናንስ ሚኒስትሮች የኢጋድ የኮሮናቫይረስ የድንገተኛ ምላሽ ፈንድ መቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጥናት እንዲያድርጉ በመሪዎቹ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል።

የኢኮኖሚ ጉዳቱን አስመለክቶ የሚደረገው ጥናት ከፋይናንስ ተቋማትና ከልማት አጋሮች የፋይናንስ ድጋፍ ማግኘት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ተመልክቷል።

የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከቀናት በፊት በደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳ ሊቀመንበርነት የሚመራው የአፍሪካ አገሮች መሪዎችና መንግስታት ጠቅላላ ቢሮ ያደረገው በቴሌኮንፍረንስ ካደረገው ውይይት የተገኘውን ውጤት አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከውይይቱ በኋላ ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚያስችል ፈንድ ለማቋቋም ከስምምነት ላይ መደረሱንና የቢሮው አባል አገሮች 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በፍጥነት ድጋፍ ለማድረግ መስማማታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ቢሮው የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጣር ማዕከል (ሲዲሲ) ቫይረሱን ለመከላከል ለሚሰራው ስራና አቅሙን ለማሳደግ የ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ መስማማቱን አውስተዋል።

''ኬንያ ለጎረቤት አገሮች አቅሟ በፈቀደው መጠን ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ለሚሰሩት ስራ ድጋፍ ታደርጋለች'' ብለዋል።

የኢጋድ አባል አገሮች ኮቪድ-19ን ለመከላከል ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ በቀጠናው እየሰፋ ያለውን የአንበጣ መንጋ መከላከል ላይም ትኩረት አድረገው መስራት እንዳለባቸው ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም