በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለኮሮና ቫይረስ መከላከል 110 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ እየተሰራ ነው

72

አሶሳ፤ መጋቢት 21 / 2012 ( ኢዜአ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ሥራ የሚውል 110 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ የተጀመረው ጥረት ለማሳካት ሁሉም እንዲረባረብ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥሪ አቀረቡ፡፡

የክልሉ የኮሮና ቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል በበሽታው መከላከል ዙሪያ በአሶሳ ከተማ ተወያይቷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አቶ አሻድሊ ሃሰን እንደገለፁት ገንዘቡ  የሚሰበሰበው በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ለውሃ አቅርቦትና ለንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች አቅርቦት ለማዋል ነው።

በሽታውን ለመከላከል የተከፈቱ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት በህክምና ቁሳቁሶች ለማጠናከርም ገቢው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል ።

በገቢ ማሰባሰብ ሂደቱ 62 ሚሊዮን ከክልል ቢሮዎች እና 48 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከወረዳ መስሪያ ቤቶች እንደሚጠበቅ የገለጹት አቶ አሻድሊ ባለሃብቱ ፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ አርሶ አደሩ፣ የመንግስት ሠራተኛውና ሁሉም አካላት አቅማቸው በፈቀደ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከግብረ ኃይሉ አባላት መካከል አቶ ይስሃቅ አብዱልቃድር  በበኩላቸው  " በኛ  ባህል ህዝቡ ካልተጨባበጠ ሰላምታ የሰጠ ስለማይመስለው ይሄ ለጊዜው መቆም አለበት" ብለዋል።

በሽታውን ለመከላከል የኃይማኖት አባቶች በየፊናቸው እያስተማሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በሽታውን ለመከላከል በተለይ  ቀበሌና ጎጥ ድረስ በመውረድ መስራት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የግብረ ኃይሉ አባል ሼህ እንድሪስ አህመድ ናቸው።

ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ በበኩላቸው በሽታውን ለመከላከል አሁን ባለው ሁኔታ  በአካባቢው ያለስራ ወደ ገበያ የመሄድ ሁኔታ የተለመደ በመሆኑ ይህ መቅረት እንዳለበት አመልክተዋል።

ከአካላዊ ንኪኪ በመራቅ ረገድ ለውጥ እንዳልመጣና ከፍተኛ መዘናጋት እንደሚታይ ተገልጿል።

ህብረተሰቡ እራሱን በመጠበቅ በሽታውን በመከላከል ረገድ አጠራጣሪ ምልክቶች ሲመለከት ጥቆማ በመስጠት  የድርሻውን እንዲወጣም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም