የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር የሶስትዮሽ ውይይቱን ዳግም ሊያስጀምሩ ነው

67

መጋቢት 21/2012 የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽን የሶስትዮሽ ውይይት ዳግም መጀመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር በቅርቡ በኢትዮጵያና በግብጽ ጉብኝት እንደሚያደርጉ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስቴቨን ሙንቺን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በስልክ ውይይት ማድረጋቸውን የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በውይይቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚካሄደውን ውይይት ለማስቀጠልና ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ በኢትዮጵያና በግብጽ ጉብኝት ለማድረግ እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በዋሺንግተን ዲሲ ሲካሄድ የነበረው ውይይት አገሮቹ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ እንዲደርሱ ማድረጉንና ውይይቱን ማስቀጠል አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሁለቱ ወገኖች የግድብ ጉዳይ በጣም አንገብጋቢ በመሆኑ ዓለም ለኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ መፍትሔ ከሰጠ በኋላ ውይይቱ መቀጠል እንዳለበት የጋራ መግባባት ላይ እንደደረሱም ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአገር ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምታደርገውን ውይይት ባለማጠናቀቋ ምክንያት የካቲት 19 እና 20 ቀን 2012 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ ሊካሄድ በነበረው የሶስትዮሽ ውይይት ላይ እንደማትሳተፍ ማሳወቋ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም