የትጥቅ ትግል ሲያደርግ የቆየው የተባበሩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር አባላት አዲስ አበባ ገቡ

135
አዲስ አበባ ሰኔ 24/2010 መቀመጫውን በውጭ አድርጎ የትጥቅ ትግል ሲያካሄድ የቆየውና "የተባበሩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር" በሚል የሚጠራው የፖለቲካ ማህበር አመራር አባላት በአገር ውስጥ ሰላማዊ ትግል ለመጀመር በመወሰን ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብተዋል። በግንባሩ ሊቀመንበር አባ ነጋ ጃራ ለታና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ብርጋዴር ጄኔራል ሐይሉ ጎንፋ የተመራውን ቡድን  የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌና ሌሎች  የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በመገኘት ተቀብለዋቸዋል። የተባበሩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ተገንጥሎ የተቋቋመ ደርጅት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መቀመጫቸውን በውጭ አገራት አድርገው በተለያየ መንገድ የተቃውሞ ፖለቲካ የሚያራምዱ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው በመመለስ በአገሪቷ የፖለቲካ እንቀሰቃሴ ውስጥ በሰላማዊ ትግል እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። የግንባሩ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ብርጋዴር ጄኔራል ሐይሉ ጎንፋ ግንባሩ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ከመንግስትና ከህዝብ የተደረገውን ጥሪ በመቀበል በሰላማዊ መንገድ ለመታገል እንደሆነ ይገልጻሉ።  በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ እየታየ ያለውን ለውጥ እንደሚያደንቁ የሚናገሩት ብርጋዴር ጄኔራል ሐይሉ ግንባሩ ከተለያዩ አካላት ጋር በመወያያትና መሻሻል ባለባቸው የመንግስት ፖሊሲዎች ላይ ሀሳብ በማመንጨት በአገሪቷ የተለያዩ ጉዳዮች መሳተፍ እንደሚፈልግም ተናግረዋል። ባለፉት ሶስት ወራት በተወሰዱት እርምጃዎች የታየው ጅማሪ ለውጥ ተጠናክሮ እንዲጠቀጥል ድርጅታቸው ከመንግስትና ህዝብ ጋር በትብብር እንደሚሰራም ብርጋዴር ጄኔራል ሐይሉ ገልፀዋል። የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው የተባበሩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የትጥቅ ትግሉን  በመተው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መወሰኑ የሚበረታታ ነው ይላሉ። አስካሁን ወደ አገር ቤት የመጡትና ወደ ፊትም የሚመጡት ፓርቲዎች ጋር ውይይት ለማድረግ አቅደዋል ብለዋል። ፓርቲዎቹ በአገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት በሚቻልበት መንገድ ለሚያነሷቸው ሃሳቦች መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች እንዳሉም ተናግረዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቷ የፖለቲካ ምህዳር መስፋት ላይ የበኩላቸውን ገንቢ ሚና ይወጣሉ ብሎ መንግስት እንደሚያምንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል። በቅርቡ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/ አመራሮች፣ የቀድሞ የኦህዴድ መስራችና የሥራ አስፈጻሚ የነበሩ አቶ ዮናታን ዲቢሳና የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩት ኮሎኔል አበበ ገረሱ እንዲሁም የደርግ ባለስልጣን የነበሩት አምባሳደር ዶክተር ካሳ ከበደና በአሜሪካ የ’ሞረሽ ለወገኔ’ የአማራ ሲቪክ ማህበር መስራች አቶ ተክሌ የሻው የመንግስት ጥሪን ተቀብለው ወደ አገራቸው መመለሳቸው የሚታወስ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም