ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኮቪድ19 ዙሪያ ከኢጋድ አመራሮች ጋር ተወያዩ

59

መጋቢት 21/2012( ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከምሥራቅ አፍሪካ ክልላዊ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አመራሮች ጋር በኢንተርኔት የታገዘ ውይይት አካሂደዋል።

በዚህም ኮቪድ-19 በዓለም አቀፍ ደረጃ እያስከተለ የሚገኘውን ፈታኝ ሁኔታ ለመቋቋም እንዲቻል፣የጋራ አመራር እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ከአመራሮቹ ጋር መስማማታቸውን ገልፀዋል፡፡

"ቫይረሱ በጤና ሥርዓታችን እና በኢኮኖሚያችን ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ በየግላችን ለመቋቋም ከባድ ነው" ሲሉ ነው የጠቀሱት፡፡

ቫይረሱ እንደ ቱሪዝም ያሉ በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ጫና ማሳረፉም ተገልጿል።

ስለዚህ ሁኔታውን ለመቋቋም "በጋራ ድጋፍን ማፈላለግ፣ እያንዳንዳችን በቀላሉ ልናገኛቸው የምንችላቸውን ግብአቶች መጋራት፣እንዲሁም በቅርበት ሆኖ ልምድ መለዋወጥ ዓይነተኛ መፍትሔ" ስለመሆኑ ነው የተናገሩት፡፡

ሀገራት ያስመዘገቡት የኢኮኖሚ ዕድገት ለጉዳት የተጋለጠ በመሆኑ፣ሁኔታውን በአሸናፊነት ለመወጣት የምቻለው በጋራ አመራር እና በተቀናጀ ተግባር ብቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፤ተስፋን መሰነቅ፣በዕቅድ መመራትና ተባብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ከፌስቡክ ገፃቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም