ለአሶሳ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ሊፈተሽ ይገባል... የከተማዋ ነዋሪዎች

69
አሶሳ ሰኔ 24/2010 የአሶሳ ነዋሪዎች በከተማው የተከሰተውን የፀጥታ ችግር በዘለቂነታ ለመፍታት ከችግሩ ጀርባ ያሉ አካላት እንዲጠየቁና የክልሉ የፀጥታ መዋቅር እንዲፈተሽ ጠየቁ። ነዋሪዎቹ በትላንትናው እለት ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ የከተማውን ጸጥታ ዘላቂነት ለማረጋገጥ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ እንዲዋቀርም ጠይቀዋል። በወይይቱ የተሳተፉት አቶ ተሾመ ፀጋ በከተማዋ የፀጥታ ችግር በተከሰተበት የመጀመሪያ ሁለት ቀናት አመራሩና የፀጥታ አካላት በአፋጣኝ ችግሩን ለመፍታት ባለመንቀሳቀሳቸው መባባሱን ተናግረዋል፡፡ የከተማዋ የፀጥታ ችግር እንዲባባስ ያደረጉና የተሳተፉ የፀጥታ አካላትና አመራሮችን በማጣራት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም ችግሩ እንዳይፈጠር ከየአካባቢው ነዋሪዎች የተወሰኑ ግለሰቦችን በመምረጥ የከተማቸውን እንቅስቃሴ ከፀጥታ አካሉ ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡፡ በከተማዋ ከአርባ አመት በላይ እንደኖሩ የገለፁት አቶ ሊጋባ ጃለታ በበኩላቸው አሶሳ ነዋሪዎች በፍቅርና በመተሳሰብ በጋራ የሚኖሩባት ከተማ እንደሆነች ተናግረዋል፡፡ የተከሰተው ችግር አብዛኛውን የከተማዋን ነዋሪዎች የማይወክል በመሆኑ ህዝቡ ተቀራርቦ በመወያየት ሊፈታው እንደሚገባ አስተያየት ሰጥዋል፡፡ በከተማዋ ችግር ሊከሰት እንደሚችል ህዝቡ ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ ሲያነሳ እንደነበር በመግለጽ ለጉዳዩ በቂ ተኩረት ባለመሰጠቱ የፀጥታ ችግሩ ሊከሰት እንደቻለም ተናግረዋል፡፡ የከተማዋን የፀጥታ ችግር ለማባባስ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን የያዙ አካላት በመኖራቸው አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ እርምጃ እንዲወሰድም ጠይቀዋል፡፡ ወጣት ሽመልስ ገናናው የተባለ የከተማዋ ነዋሪ በከተማዋ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ሊባባስ የቻለው የክልሉ የፀጥታ አካላት የሚጠበቅባቸውን ያክል በገለልተኛነት ለማረጋጋት ባለመስራታቸው እንደሆነ ገልጿል፡፡ “በከተማዋ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት በፀጥታ መዋቅሩ ችግር ያለባቸው አመራርና አባላት ላይ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል” ብሏል፡፡ የፀጥታ ችግሩ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንዳይከሰት አሁንም ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም ገልጿል፡፡ አቶ አለማየሁ መልካሙ በሰጡት አስተያየት በፍቅርና በመተሳሰብ አብረው በሚኖሩ ማህበረሰቦች መካከል የተፈጠረው ችግር በሌላ አካላት ተቀነባበረ ነው የሚል እምነት እንዳለቸው ገልፀዋል፡፡ ተለያይቶ ሊኖር የማይችል ህዝብ በመሆኑ ከሁሉም ማህበረሰብ የተወጣጣ ኮሚቴ በማዋቀር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሊሰራም እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ርዕሠ-መስተዳድር አቶ አሻድ ሃሰን “የአሶሳ ከተማ የብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያ በመሆኗ የፀጥታ ችግር ሲፈጠር የማይነካ የኢትዮጵያ አካባቢ አይኖርም” ብለዋል፡፡ “በክልሉ የሚኖሩ ህዝቦችም ከክልሉ ብሄረሰቦች ተለይተው የማይታዩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝቦች ናቸው” ብለዋል፡፡ የተፈጠረው ችግር በፍቅርና በአብሮነት ሲኖሩ የነበሩትን የክልሉን ህዝቦች እንደማይወክል ገልጸው በችግሩ የተሳተፈ አመራርም ይሁን ማንኛውም ግለሰብ ከተያቂነት እንደማያመልጥ አስታውቀዋል፡፡ በክልሉ የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት የሚሞክሩ አካላት እየመጣ ያለውን ለውጥ የማይፈሉጉ ኃይሎች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ የከተማዋን ብሎም የክልሉን ሠላም ለማስጠበቅ የክልሉ ነዋሪዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም