የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኮሮናን ለመከላከል ለሚከናወነው ስራ አምስት ሚሊዮን ብር ለገሰ

73

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2012 ( ኢዜአ) የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ለሚከናወነው ተግባር የሚውል  የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

ፕሬዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴም የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመስጠት ወስነዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መገኘቱን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመቋቋም የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል፡፡

ለዚህ ስኬታማነትም በአገር ውስጥ እና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በዓይነትም ሆነ በገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማትም ይህንኑ ጥሪ ተከትለው ድጋፍ እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል።

በዛሬው ዕለትም የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት 'የበጀት ዓመቱ ለመጠናቀቅ በሚቀሩት ሶስት ወራት ውስጥ ለሚኖሩት ሥራዎች የሚያስፈልገውን ወጪ በማብቃቃትና በቁጠባ በመጠቀም' ከተመደበልኝ መደበኛ በጀት የሚቀነስ የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለዚህ አገራዊ ጥሪ እሰጣለሁ ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመስጠት መወሰናቸውን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው "እንደ አገር የመጣውን ችግር ለመቋቋም የሚቻለው፤ በጋራ እና በጽናት በመቆም እንደሆነ ስለሚገነዘብ ነው" ብሏል ባወጣው መረጃ።

ጽህፈት ቤቱ በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ ሁሉም ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን በቀጣይም የሚጠበቅበትን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም