በትግራይ ክልል በፖሊስ በተተኮሰ ጥይት የአንድ ወጣት ህይወት አለፈ

61

መቀሌ፤ መጋቢት 20/2012(ኢዜአ) በትግራይ ክልል ናዕዴር አዴት ወረዳ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ተከትሎ የተከለከሉ እንቅስቃሴዎችን በማስቆም ሂደት ባጋጠመ ግጭት የአንድ ወጣት ህይወት መጥፋቱን የወረዳው ፖሊስ አስታወቀ።   

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ኪዳነ የማነ እንደገለጹት በክልሉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የወረዳው የፖሊስ አባል በመጠጥ ቤት የተሰበሰቡ ወጣቶችን ለመበተን ሲሞክር በተፈጠረ ግርግር በተተኮሰ ጥይት የወጣቱ ሕይወት ሊያልፍ ችሏል።

ፖሊስ ሁኔታውን በሰከነ መንገድ ማረጋጋት ሲገባው ተቀባይነት የሌለውና ከአንድ ፖሊስ የማይጠበቅ ህግና ህሊና የማይፈቅደውን ተግባር በመፈጸሙ በህግ እንደሚጠየቅም  ገልፀዋል።

የግድያ ወንጀሉን የፈፀመው የፖሊስ አባልም በቁጥጥር ስር መዋሉንና ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነ ኢንስፔክተር ኪዳነ መናገራቸውን ከወረዳው የህዝብ ግንኙነት ፅሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም