የሀገር መከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ኮማንድ ፖስት ኮሮናን ለመከላከል በትኩረት እየሰራ ነው

217

አዲስ አበባ መጋቢት 20/2012(ኢዜአ) ኮሮናቫይረስ እንዳይዛመት በትኩረት እየሰራ መሆኑን በሀገር መከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ወረርሽኙን ለመከላከል የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።

የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ተወካይና የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄነራል ይልማ መኳንንቴ እንዳሉት፤ ኮማንድ ፖስቱ የመከላከያ ስራው ቀልጣፋና ተደራሽ እንዲሆን በስሩ በተቋቋሙ ቡድኖች እየሰራ ይገኛል።

በሽታው በሰራዊቱ ውስጥ ቢከሰት ተጨማሪ የጤና ሙያተኞችን ለመጠቀም ከመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት መታቀዱንም ሰብሳቢው ገልጸዋል።

በመሆኑም የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች እንደ ብሄራዊ ግዳጅ ዝግጁ የማድረግ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

እንደ ሀገር የህክምና መሳሪዎች ግብዓት እጥረት እንዳለ ጠቅሰው በግዥና ከጤና ሚኒስቴር የተገኙ የበሽታ መከላከያ ቁሳቁሶችም ለሰራዊቱ ክፍሎች ተደራሽ ይደረጋሉ ብለዋል።

በተለይም የህክም መከላከያ አልባሳትና ሰራዊቱ የሚጠይቃቸው የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እንደ ቅደም ተከተላቸው ተደራሽ እንደሚደረጉ ነው የተናገሩት።

ቫይረሱ ቢከሰት እንኳን ለመከላከል እንዲቻል አደረጃጀቶችን ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑንም ኮማንድ ፖስቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።

በጦር ሃይሎች ሆስፒታል የሙቀት መለኪያ ማሽን አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝና ወደ ሆስፒታሉ የሚመጣ ማንኛውም ሰው ምርመራ እንደሚደረግለት የሆስፒታሉ አስተባባሪ ብርጋዴር ጄኔራል ሸዋዬ ሃይሌ ገልጸዋል።

በቀጣይም በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ስፍራዎች የሙቀት መለኪያ ማሽኖችን ለመጠቀም መታቀዱን አብራርተዋል።

የመከላከያ ጤና ማበልጸግና በሽታን መከላከል መምሪያ ሃላፊ ኮለኔል ዶክተር ሃደገይ አያሌው በበኩላቸው፣ ሰራዊቱ በሽታን የመከላከል ልምድ ቢኖረውም ከመንግስት ተቋማት የሚሰጡ የጥንቃቄ መመሪያዎችን ተግባራዊ እንዲያደረግ አስገንዝበዋል። 

ሰራዊቱ ስለበሽታው መከላከል በተመለከተም ከመንግስት ተቋማት ውጭ በሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎች መዘናጋት እንደሌለበት አሳስበዋል።

በካምፖች የውሃ እጥረት ችግሮችን ለመቅረፍም ሁሉም መምሪያዎች ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም