የባህር ዳሩ የድጋፍ ሰልፍ በሰላም ተጠናቀቀ

85
ባህር ዳር ሰኔ 24/2010 "ለውጥን እንደግፍ ዴሞክራሲን እናበርታ" በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳር ከተማ ዛሬ የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በሰላማዊ መንገድ ተጠናቀቀ። በድጋፍ ሰልፉ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችና የሃይማኖት አባቶች ታዳሚ ሆነዋል። በድጋፍ ሰልፉ ላይ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡ ወዲህ ያስመዘገቧቸውን ሁለንተናዊ ለውጦች የሚደግፉ የተለያዩ መፈክሮችን ሰልፈኞች ይዘው አንጸባርቀዋል። ዛሬ ጠዋት በባህር ዳር ከተማ ብሔራዊ ስታዲየም በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከክልሉና ከመላ ኢትዮጵያ የተውጣጡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ እትዮጵያዊያን ተሳትፈዋል። በድጋፍ ሰልፉ ላይ ኢትዮጵያዊነት፣ መደመር፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ መተሳሰብና አብሮነትን የሚሰብኩ ሙዚቃዎች ተዘምረዋል። በድጋፍ ሰልፉ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያዊነትንና አገራዊ መግባባትን በመፍጠር በኩል ላስመዘገቡት ተጨባጭ ለውጥ ምስጋና የሚቸሩና ከጎንህ ነን የሚሉ መልክቶች በስፋት ተላልፈዋል። ወጣቶች እርስ በእርስ በመተጋጋዝና በማስተባበር ያዘጋጁት የድጋፍ ሰልፍ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላማዊ መንገድ ተጠናቋል። በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለታዳሚዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም