በአዳማ ከተማ የታክሲ ትራንስፖርት ታገደ

86

አዳማ መጋቢት 20/2012 (ኢዜአ) በአዳማ ከተማ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ከዛሬ ጀምሮ እንዳይንቀሳቀሱ መታገዳቸውን የከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ።

በሌላ በኩል ደግሞ መመሪያን ተላልፈው የተገኙ የተለያዩ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱም ተመልክቷል።

የባለስልጣኑ ኃላፊ አቶ አበራ አብዲሳ ለኢዜአ እንደገለጹት  ተሸከርካሪዎች እንዳይንቀሳቁ የታገደው   በሽታው አሳሰቢ በመሆኑ ህብረተሰቡን ለመታደግ የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ ዛሬ ካቢኒያቸውን ሰብሰበው በጋራ በወሰኑት መሰረት ነው።

በውሳኔው መሰረት ከዛሬ ጀምሮ በአዳማ ከተማ የሚገኙ ባጃጅና ሚኒባስ ጨምሮ ከ10ሺህ በላይ ለህዝብ የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ላልተወሰነ ጊዜ መታገዳቸውን አስታውቀዋል።

እገዳውን  ተላልፈው በሚገኙ አሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወሰድም አስጠንቅቀዋል።

ይህንን የሚያስፈጽሙ የክልሉና ፌዴራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ኃይልና ሌሎች የህግ አስከባሪዎች መሰማራታቸውንም አመልክተዋል።

ህብብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ በእግር ሲጓዝ ከአካል ንክኪ በመራቅ እራሱን እንዲጠብቅም መልዕክት አስተላልፈዋል።


በሌላ በኩል ደግሞ እንዲዘጉ መንግስት ያወጣውን መመሪያ ተላልፈው የተገኙ የመጠጥ፣ የምግብ፣ የምሽት ጭፈራና ጫት ቤቶች መታሸጋቸውን የገለጹት ደግሞ የከተማው አስተዳደር ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዮሚ አበጃ ናቸው።

እንዲሁም የግብርን ምርቶች፣ የንጽህና መጠበቂያና ሌሎች ሸቀጦች ላይ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ ጨምረው የተገኙ መድኃኒት ቤቶች ጨምሮ 23 የተለያዩ የንግድ ድርጅቶች ላይም ተመሳሳይ እርምጃ መወሰዱንም አስረድተዋል።

በቀጣይም  መመሪያን ተላልፈው በሚገኙ የንግድ ድርጅቶች ላይ የሚደረገው ቁጥጥርና የሚወሰዱ እርምጃዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቁት ኃላፊዋ ሀብረተሰቡም ህግን የሚተላለፉትን በመጠቆምና እራሱን ከበሽታው በመጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም