በሕዝብ ጤና ላይ ሽብር በሚነዙ አካላት ላይ ህግ አስከባሪዎች ተግባራቸውን በጥብቅ እንዲወጡ ትእዛዝ ተሰጠ

64

አዲስ አበባ መጋቢት 20/2012(ኢዜአ) በሕዝብ ጤና እና ደኅንነት ላይ በልዩ ልዩ መንገድ ሽብር የሚነዙ አካላት ላይ የህግ አስከባሪ አካላት ሕግ የማስከበር ተግባራቸውን በጥብቅ እንዲያከናውኑ ትእዛዝ ተላለፈ።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የጤና ቀውስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከሰት፣ የተሳሳተ መረጃን ተቀብሎ ማሰራጨት ከቀውሱ እኩል ጎጂ መሆኑን አመላክቷል።

በመሆኑም ማንኛውም ሰው እንዲህ ባለ ጊዜ የሐሰት ዜናዎችን ለማስቆም የሚችለውን ሁሉ ማድረግ አለበት ብሏል።

የፌደራል መንግሥት ኮቪድ-19ን በተመለከተ በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት፣ መረጃን የማደራጀት እና በየዕለቱ የማሠራጨት ሥራን እያከናወነ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣው ኮሚቴ እና ሌሎች ዐበይት ኮሚቴዎች ያላቸውን ወቅታዊ የሥራ ክንውን እያስተባበረና መረጃን እያስተላለፈ መሆኑ ይታወቃል።

ሕዝቡ እንዲህ ባለው አስከፊ ጊዜ የፓለቲካ ትርፍ ለማግኘት ከሚንቀሳቀሱ አካላት ነቅቶ ራሱን እንዲጠብቅ ተጠይቋል።

የኅብረተሰብ ጤና መረጃን ማዛባት እና በዜጎች መካከል ፍርሐት እና ረብሻን መንዛት በወንጀል የሚያስጠይቅ ሀገራዊ አንድነትን የማናጋት ተግባር መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል።

በኮቪድ19 ላይ መረጃን የሚሰጡ ዐበይት አካላት የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት መሆናቸውንም አመልክቷል።

በዚህ ፈታኝ ወቅት በሕዝብ ጤናና ደኅንነት ላይ በልዩ ልዩ መንገድ ሽብር የሚነዙ አካላት ላይ የሕግ አስከባሪ አካላት ሕግ የማስከበር ተግባራቸውን በጥብቅ እንዲያከናውኑ የታዘዙ መሆኑንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም