የምዕራብ ኦሮሚያ ሰላም በመሻሻሉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው-- የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ

142

አዲስ አበባ መጋቢት 20/2012(ኢዜአ) በምዕራብ ኦሮሚያ የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ በአካባቢው የልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ። 

ፕሬዚዳንት ሺመልስ አብዲሳን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ይገኛሉ።

በምዕራብ ኦሮሚያ በተለይ ቄለምና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ከፍተኛ የጸጥታ ችግር የነበረባቸው አካባቢዎች በመሆናቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት  የልማት ሥራ ተቋርጦ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት ግን በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም በመፈጠሩ የልማት ሥራዎች መጀመራቸውን ፕሬዚዳንቱ አቶ ሽመልስ ገልጸዋል።

ምዕራብ ኦሮሚያን የአትክልትና የፍራፍሬ ምርት ማእከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በአካባቢው አቮካዶ፣ ማንጎና ቡናን በስፋት ለማምረት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት 1 ሚሊዮን የቡና እንዲሁም 26 ሺህ የአቮካዶ ችግኞች ተዘጋጅተው በምዕራብ ኦሮሚያ ላሉ ዞኖች ለማከፋፈል ዝግጅት ተደርጓል።

የዶንቢዶሎ አየር ማረፊያ የማስፋፊያ ሥራ፣ የደንቢዶሎ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ የነጆ ሰብስቴሽን እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ሥራዎችም በክልሉ አመራሮች ተጎብኝተዋል።

በአካባቢው በነበረው የሰላም ዕጦት የልማት ሥራዎች ተቋርጠው መቆየታቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳቱ ህዝብና መንግስት ባደረጉት ርብርብ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።

የተፈጠረው ሰላም ዘላቂ ይሆን ዘንድ ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም እገዛውን እንዲያጠናከርም ጠይቀዋል።

መንግስትም በአካባቢው ተጨማሪ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በአካባቢው ተቋርጦ የቆየው የስልክ አገልግሎትም በቅርብ ጊዜ ኔትወርኩ እንደሚለቀቅ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ ከጉብኝታቸው ጎን ለጎን የደምቢዶሎ፣ ነጆ፣ ጊምቢ እና ነቀምቴ ነዋሪዎችን አወያይተዋል።

የየአካባቢው ነዋሪዎችም የውሃ፣ ኤሌክትሪክ እንዲሁም ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉላቸው ጠይቀው ከፕሬዚዳንቱ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም