የኮሮና ቫይረስ የቅድመ ጥንቃቄ መመሪያዎችን በመጣስ የህዝብን ጤንነትና የአገር ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተባለ

57

መጋቢት 19/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ(ኮቪድ-19) የቅድመ ጥንቃቄ መመሪያዎችን በመጣስ የህዝብ ጤንነትና የአገር ደህንነትን አደጋ ላይ በሚጥሉ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለ፣ በአህጉራችን አፍሪካ፣ እንዲሁም በሃገራችን ኢትዮጵያ ትልቅ ስጋት የደቀነ ወረርሽኝ እንደሆነ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በአሁኑ ወቅትም ይህን ወረርሽኝ መግታት እና መከላከል ትልቅ ሃገራዊ የትኩረት አጀንዳ እንደሆነም ገልጿል። 

እስካሁን በተለያዩ ሃገራት የተከሰተውን የወረርሽኙን ስርጭት፣ እንዲሁም የዓለም ጤና ድርጅት እና የአገራችን የጤና ባለሞያዎች እና ተቋማት የሚያቀርቧቸውን ሙያዊ መረጃዎች እና ምክሮች ከግምት በማስገባት መንግስት ወረርሽኙን ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል።

ህዝቡ ስለበሽታው መረጃ ኖሮት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዲችል ስለወረርሽኙ ባህሪያት እና መተላለፊያ መንገዶች በየጊዜው ከሚሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በተጨማሪ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የጥንቃቄ እርምጃዎች በየደረጃው እንዲወሰዱ መንግስት ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን መመሪያዎችም ተሰጥቷል።

ይሁንና እነዚህን ውሳኔዎች እና መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ እስካሁን ያለው ሁኔታ በቂ እና አስተማማኝ ነው ለማለት እንደማይቻል የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል።
ይህን ሁኔታ ለመለወጥ አስፈላጊው መረጃ ለህዝቡ እንዲደርስ የሚደረገው ጥረት ተጥናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ነገር ግን ሆን ብለው እና ለህዝብ ደህንነት እጅግ አደገኛ በሆነ መልኩ አግባብነት ባላቸው የመንግስት መዋቅሮች የሚሰጡ መመሪያዎችን እየጣሱ ያሉ ግለሰቦች እና ተቋማት እንዳሉ ለማወቅ መቻሉ ተገልጿል።

ሆን ብለው ወረርሽኙን በተመለከተ አደገኛ የሃሰት መረጃ በማሰራጨት ህዝብን በሚያሸብሩ፣ እንዲሁም በዚህ አጋጣሚ አላግባብ የሆነ ትርፍ ለማካበት የአቅርቦት እጥረት የሚፈጥሩ ግለሰቦች እና ተቋማት ከሕገ -ወጥ ተግባራቸው እንዲታቀቡ አሳስቧል።

የኮሮና ቫይረስ የቅደመ-ጥንቃቄ መመሪያዎችን በመጣስ የህዝብን ጤንነት እና የአገርን ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ እንዲሁም የኮሮና ቫይርስ ስጋትን ሰበብ አድርገው ሆን ብሎ ህዝብ የማሸበር ወንጀል በሚፈጽሙ ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም ገልጿል።

የኮሮኖ ቫይረስ ስርጭትን አስመልክቶ የሚሰጡ የጥንቃቄ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ጥቅሙ በቅድሚያ ለራስ፣ ቀጥሎም በዙሪያችን ላሉ ቤተሰቦቻችን፣ ወገኖችን እና ብሎም ለአገር ነው በሏል ጠቅላይ አቃቤ ህግ። 

የዜጎችን ህይወት እና ጤና እንዲሁም የአገርን ህልውና እና ደህንነት አደጋ ላይ የጣለውን የዚህን ወረርሽኝ ስርጭት ለመመከት የሁሉም ጥረት እና ትብብር እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም መግለጫው አትቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም