የተጀመሩ ምርምሮች ቀሪ ስራዎች ስላላቸው ህብረተሰቡ ራሱን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል ጥንቃቄ ከማድረግ መዘናጋት እንደሌለበት ተገለጸ

110

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2012 (ኢዜአ)የተጀመሩ ምርምሮች ቀሪ ስራዎች ስላላቸው ህብረተሰቡ ራሱን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል ጥንቃቄ ከማድረግ መዘናጋት እንደሌለበት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገለጸ። 

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክረታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ የተጀመሩ የምርምር ስራዎች ተስፋ ያላቸው ቢሆንም ቀሪ ስራዎች አሉት።

ከውጭ አገር የሚመጡ ሰዎችን ለይቶ ለማቆየት የሚያስችሉ ተቋማት መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።

የሃይማኖት ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ ግለሰቦችና ሌሎች ተቋማት በዚህ ረገድ ዝግጅት እንዳደረጉ ገልጸው፤ተቋማቱ ያደረጉት ዝግጅት በኮሚቴ እየተገመገመ እንደሆነም ተናግረዋል።

እስካሁን ድረስ ከግለሰቦችና ከተቋማት 47 ሚሊዮን ብር መሰባሰቡን የገለጹት አቶ ንጉሱ፤ ድጋፉን በማዕከል ለማድረግና ለማቀናጀት የተዘጋጀው ኮሚቴ በአይነትም ሆነ በገንዘብ ተጨማሪ ገቢ ለማሰባሰብ በሚሌኒየም አዳራሽ ቦታ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ድጋፍ ለማድረግ የጥሪ ስልክ ቁጥሮች መዘጋጀታቸውን ተናግረው፤ በውጭ አገር ኤምባሲዎች የሚገኙ ሰራተኞች የቁሳቁስ ድጋፍ እያሰባሰቡ መሆኑን ገልጸዋል።

የድጋፍ ሂደቱን አጋጣሚ በመጠቀም ለማጭበርበር የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸውን በመግለጽ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት በሙሉ መንግስት ያቋቋመውን ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ብቻ እንዲጠቀም አስገንዝበዋል።

የጸጥታ አካላት ልዩ ልዩ ግብረሃይል አቋቁመው በየደረጃው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ንጉሱ፤ ህዝቡን ለማዳን የሚያስችል ቁመና ላይ እንዲገኙ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መሰራቱንም ገልጸዋል።

በትናንትናው እለት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በጤና ሚኒስቴር በኩል የኮሮናቫይረስን መከላከል የሚያስችል የምርምር ስራ መገለጹን ያስታወሱት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊው፤ ተመራማሪዎቹ የደረሱበት ደረጃ ተስፋ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።

ነገር ግን ቀሪ ስራዎች በመኖራቸው ህብረተሰቡ የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት በማሳሰብ፤ የቫይረሱ ስርጭት ጊዜ የማይሰጥ መሆኑን በማስተዋል መዘናጋት መፈጠር እንደሌለበት ገልጸዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ እያገዙ ላሉ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል።

ለብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ በሚሌኒየም አዳራሽ በአይነትም ሆነ በገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት በሚከተሉት የስልክ ቁጥሮች ጥሪ በማድረግ ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ።

+251111552171

+251115539474

+251966942712

+251911220703

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም