ኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ከቻይና ጎን መቆሟ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል … አምባሳደር ታን ጂያን

704

መጋቢት 19/2012 (ኢዜአ)ኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ከቻይና ጎን መቆሟ የሁለቱን አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክር በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን ገለጹ። 
የኮሮናቫይረስ በቻይና ግዛት ሁዋን ለመጀመሪያ ጊዜ መከሰቱን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።  

አምባሳደር ታን ጂያን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ቫይረሱን በመከላከሉ ረገድ ኢትዮጵያ ለቻይናዊያን ያሳየችው አጋርነት የሚያስመሰግናት ነው።   

ይህ ጉዳይ ቻይናዊያን በልባቸው ያስቀመጡት ትልቅ አስተዋጽኦ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።  

ኢትዮጵያና ቻይና ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ አጋርነት እንዳላቸው የገለጹት አምባሳደሩ፤ ”መሰል የአገሮቹ መደጋገፍ በቀጣይ የሚሰሩ የትብብር ስራዎችን ወደ ላቀ ምዕራፍ ያሸጋግራሉ” ብለዋል።

የኮሮናቫይረስ ዓለም አቀፍ ስጋት መሆኑን ጠቁመው የአገሮቹ ግንኙነት የኀብረተሰብ ጤና ማስጠበቅን ቅድሚያ የሚያደርግ ነው በማለት አስረድተዋል። 

በተለይም በጤናው መስክ ቻይና ለአፍሪካ የምትሰጠውን ድጋፍ እንደምታጠናክር ያስታወቁት አምባሳደር ታን ጂያን፤ ”ቻይና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠሪያ ማዕከል ግንባታን ጀምራለች” ብለዋል።

በቻይና ወረርሽኙ በተከሰተ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ አለማቋረጡም አገሮቹ በብዙ መስኮች ጠንካራ ትስስር እንዳላቸው አመላካች ነው ብለዋል።   

የቻይና መንግሥትና ጃክ ማ ፋውንዴሽንን የመሳሰሉ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የህክምና ቁሳቁሶች ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ አገሮች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ያመለከቱት አምባሳደሩ፤ በተለይ ቻይና ወረርሽኙን በመከላከሉ በኩል ያገኘችውን ልምድ እያካፈለች መሆኑን ተናግረዋል። 

”ቫይረሱን በመግታት ረገድ የቻይና መንግሥት ጠንካራ አመራር ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል” ያሉት አምባሳደር ታን፤ ግልጽ አሰራር መዘርጋት፣ መረጃ በፍጥነት ተደራሽ ማድረግና ህዝቡን ማሳተፍ ቫይረሱን ለመከላከል ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸውንም አብራርተዋል። 

”ቫይረሱ ድንበር ዘለል በመሆኑ በጋራ ጥረት ሊቆም ይገባል” የሚል ሀሳብ አንስተው፤ ”የምናደርገው ትብብር የበለጠ ሊጠናከር ይገባል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።   

በበሽታው ምክንያት የሚመጣውን ኢኮኖሚያዊ ድቀት አስቀድሞ ለመከካል ዓለም አቀፉ ማኀብረሰብ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚኖርበት አምባሳደሩ ጠቁመዋል።   

በአሁኑ ወቅት ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከ134 ሺህ በላይ አገግመዋል፤ 27 ሺህ 600 የሚሆኑት ደግሞ ለህልፈት መዳረጋቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።