ከአካለዊ ንክኪ ርቆ በመንፈስና በተግባር አንድ ሆኖ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን መግታት ይገባል

79

መጋቢት 19/2012 (ኢዜአ) "ከአካለዊ ንክኪ ብንራራቅም በመንፈስና ተግባር አንድ ሆነን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን መግታት ይገባናል" ሲሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች  ጥሪ አቀረቡ።

ራስን ከመጠበቅ ባለፈ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ወገኖችን መርዳት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ግለሰቦች "ሰው ነኝ ሌሎችንም እረዳለሁ" በሚል መሪ ሃሳብ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚሰራ ኮሚቴ አቋቁመዋል።

ኮሚቴው ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በዋናነት የግንዛቤ ማስጨበጥና ሌሎች የእርዳታ ማሰባሰብ ስራዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚሰራ ነው ያስታወቀው።

ተነሳሽነቱን ወስዶ ኮሚቴውን ያዋቀሩት አቶ ኦባንግ ሜቶ ''ኮሮናቫይረስ ዘር፣ ቀለምና ኃይማኖት ሳይለይ የሰው ልጅን በስፋት እያጠቃ ይገኛል'' ብለዋል።

ኮሮናቫይረስ የተከሰተባቸው አገሮች በራሳቸው መንገድ ችግሩን ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስታውሰው፤ ''እኛ ኢትዮጵያውያን የሌሎችን እርዳታ ሳንጠብቅ ስርጭቱን መግታት እንችላለን'' ብለዋል።

''ይህ እውን እንዲሆን ግን ራሳችንን በመጠበቅ አንድ ሆነን መቆም ይገባል'' ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የመንግስት አካላት ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተው እየሰሩበት እንደሚገኙ መገንዘባቸውንም ገልጸው፤ ጉዳዩን ለመንግስት ብቻ በመተው መዘናጋት እንደማይገባ መክረዋል።

አቶ ሃብታሙ አዱኛ በበኩላቸው "በአካላዊ ንክኪ ተራራቅን ማለት አንዳችን ለሌላችን ማሰብ አቁመናል ማለት አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

ይልቁንም ከመቸውም ጊዜ በላይ የሃሳብ አንድነት እንደሚያስፈልግ ነው ያብራሩት።

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን መጻኢ እድል የሚወሰነው ዛሬ የሚሰራ የጥንቃቄ ስራ መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉም ዜጋ ይህን ታሳቢ አድርጎ እንዲንቀሳቀስ ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚቴው ስለኮሮናቫይረስ ግንዛቤ የማስጨበጡን ስራ በስፋት በመስራት የመንግስትን ጥረት እንደሚደግፍም ተናግረዋል።

ከቫይረሱ ስርጭት ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ሁኔታ የቤት ውስጥ ፍጆታ ማከማቸት ላይ የተጠመዱ ዜጎች መኖራቸውን የተናገሩት ደግሞ ዶክተር መስከረም ለቺሳ ናቸው።

በመሰል ተግባር የሚሳተፉ አካላት አቅም የሌላቸው በርካታ ወገኖች ላይ ከቫይረሱ የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱባቸው ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

''ኮሜቴው ከዚህ አንጻር በዜጎች መካከል ሰብዓዊነት እንዲሰፍን ይሰራል'' ነው ያሉት።

ኮሚቴው በተለያዩ የስራ መስክ የተሰማሩ ግለሰቦችን የያዘ ሲሆን ኮሚቴውን ዓላማ ደግፈው መቀላቀል ለሚፈልጉ ማናቸውም አካላት በሩ ክፍት መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም