የባህርዳር ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ገቢ የማሰባሰብ ስራ ጀመረ

70

ባህርዳር፤ መጋቢት 19/2012 ኢዜአ) የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ የእለት ገቢ የሌላቸው ሰዎች ለማህበራዊ ቀውስ እንዳይጋለጡ 10 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ።

በገቢ ማሰባሰቢያው ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በባህር ዳር ከተማ ምክክር ተደርጓል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና  የገቢ አሰባሳቢ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ አማረ አለሙ በምክክር መድረኩ  ላይ እንዳሉት የተጀመረው እንቅስቃሴ በሽታው  የእለት ገቢ በሌላቸው ሰዎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጫና ለመቀነስ ነው።

"በተለይም አረጋውያንና ሌሎች የእለት ገቢ የሌላቸው ሰዎችን በዚህ ወቅት ለመደገፍ 10 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል" ያሉ አቶ አማረ ለዚህም ገቢ የማሰባሰብ ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ገቢው የሚሰበሰበው በጥሬ ገንዘብ ፣ የምግብ እህልና ሌሎችም  ቁሳቁሶች እንደሆነም አመልክተዋል።

እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ ገቢው የሚሰበሰበው ከባለሃብቱ፣ ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ነው።

በአሁኑ ወቅትም በማህበራዊ አገልግሎት ግንባር ቀደም የተባሉ አካላትን የማነጋገር ስራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።

በገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት በኢትዮጵያ ንግድ፣ አቢሲኒያ፣ አባይ፣ ዳሽንና ህብረት ባንኮች የገቢ ማሰባሰቢያ ሂሳብ ቁጥር መከፈታቸውን አስታውቀዋል።

ከዚህ አስከፊ ችግር ለማዳን ሁሉም የአቅሙን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

አንዳንድ ባለሃብቶችም ለለይቶ ማቆያ የሚሆኑ ህንፃዎች መስጠት መጀመራጀውን ጠቅሰው፤ ሌሎችም ይህን አርዓያ በመከተል ሊደግፉ እንደሚገባ  ምክትል ከንቲባው አመልክተዋል።

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ ዩኒቨርሲቲው የአፍና  አፍንጫ መሸፈኛ  እጥረትን ለመፍታት በራሱ አቅም በማምረት  እያከፋፈለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከመከላከሉ ባለፈ በቫይረሱ ለተጠረጠሩ የሚሆን  የይባብና የዘንዘልማ ካምባሶችን ለለይቶ ማቆያ ማመቻቸታቸውንም ጠቁመዋል።

ካምፓሶቹ አንድ ሺህ የሚጠጉ ክፍሎች እንዳሏቸው ጠቅሰው፤ በክፍሎቹ ውስጥም ተማሪዎች ይገለገሉባቸው የነበሩ ከ7 ሺህ 400 በላይ አልጋዎች እንዳሉትም አስታውቀዋል።

የጤና ሳይንስ ኮሌጅና የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባለሙያዎች በሽታው ቢከሰት ሙያዊ  ድጋፍ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውንም  ዶክተር ፍሬው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም